
አዲስ አበባ |የካቲት 21 2015 | NBC ETHIOPIA- ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመጓጓዝ የሰው ልጆች ከባህላዊ እስከ ዘመናዊ የተለያየ አይነት መጓጓዣዎችን ይጠቀማሉ፡፡
እነዚህ መጓጓዣዎች በተለይም ዘመናዊ የሚባሉት ከሚሰጡት ከፍተኛ ጥቅም ባሻገር በአለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ መወደድ፤የመንገድ መጨናነቅ እንዲሁም የአየር ንብረት መዛባትን ጨምሮ የተለያዩ የጎንዮሽ ችግሮችን ሲያስከትሉ ይስተዋላል፡፡
ለእነዚህና ሌሎች ተጓዳኝ ችግሮች ሀገራት መፍትሔ ያሏቸውን እርምጃዎች እየወሰዱ ሲሆን ከነዚህም መካከል ሳይክልን በብዛት መጠቀም ዋነኛው መፍትሄ እየሆነ መጥቷል፡፡
በዚህ ላይ በተለይ የአውሮፓ ሀገራት ግንባር ቀደም ደረጃውን ይይዛሉ፡፡
ሀገራቱ በብስክሌት ድልድይ እንዲሁም በሰፋፊ የብስክሌት መንገድ ግንባታ የከተማ መሠረተ ልማቶቻቸውን ብስክሌትን ማሽከርከር በሚያበረታታ መልኩ መንገዶቻቸውን ማስዋብ እና መሀንባት ከጀመሩ ዋል አደር ብለዋል፡፡
በዚህም በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎቻቸውና በገነቡት የብስክሌት መሰረት ልማት ተደራሽ የሆኑ ከተሞችን እናስቃኛችኋለን፡፡
1/ኮፐንሃገን ዴንማርክ
በአለም ላይ ለብስክሌት ምቹ ከሆኑ ከተሞች አንዷ የዴንማርኳ ከተማ ኮፐንሃገን ነች ፡፡
ኮፐንሃገን 62 በመቶ የሚሆኑት ዜጎቿ ለስራ ወይም ለትምህርት በሚያደርጉት ጉዞ ብስክሌቶችን ይጠቀማሉ።
ከተማዋ በብስክሌት መሠረተ ልማት ላይ ያለማቋረጥ ኢንቨስት በማድረግና የከተማ አቀማመጧን ለብስክሌት እንዲመች በማድረግ እንደገና እየሰራች ትገኛለች።
ከብዙ የብስክሌት ምቹ መዋቅሮች መካከል፣ አራት የብስክሌት ድልድዮች ተገንብተዋል፣ በከተማዋ በርካታ የብስክሌት መሰረተልማት በመገንባት ላይ ይገኛሉ።
2/አምስተርዳም ኔዘርላንድስ
በዓለም ላይ ካሉት እጅግ በጣም ለብስክሌት ምቹ ከተሞች መካከል አንዷ ተደርጋ የምትወሰደው አምስተርዳም ነች፡፡
በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2019 ከተማዋ የብስክሌት ፓርኪንግ ቦታዎችንና ነባር መሠረተ ልማቶችን በማሻሻል ላይ የሚያተኩር የ2022 አዲስ እቅድ አውጥታ ነበር፡፡
በሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ነዋሪዎች በየዓመቱ ወደ ዋና ከተማው ስለሚፈልሱና ነባር ሳይክል ትራኮችን በማስፋት ከተማዋ ብዙ ብስክሌቶችን ለማስተናገድ አዳዲስ የብስክሌት መንገዶችን እየገነባች ነው።
በተጨማሪም ዝቅተኛ ፍጥነት ያላቸውን የሳይክል ጎዳናዎች ቁጥር በመጨመር የሳይክል ነጂዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ዋና ዋና መገናኛዎችን በመንደፍ ላይ ትገኛለች።
3/ማልሞ ስዊድን
ማልሞ ከ500 በላይ የብስክሌት መንገዶች አሏት፡፡
ከስዊድን ከተሞች ትልቋ ከተማ ማልሞ የብስክሌት አጠቃቀምን ለማስተዋወቅ የከተማዋ ዜጎች የመኪና አጠቃቀምን እንዲቀንሱ ለማድረግ የተለያዩ ዘመቻዎችን ስታደርግም ቆይታለች፡፡
ከተማዋ በከተሞች ስርአታቸው ውስጥ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ያስተዋወቀች ሲሆን ብስክሌት ነጂዎች ሲመጡ ለመኪና አሽከርካሪዎችን የሚያስጠነቅቅ ስርዓት መገንባት ይገኝበታል፡፡ ይህ ደግሞ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ከሌሎች ተሸከርካሪዎች ይልቅ ብስክሌትን እንዲመርጡ አድርጓቸዋል፡፡
4/ሞንትሪያል ካናዳ
ምንም እንኳን የአውሮፓ ከተሞች ብዙውን ጊዜ በብስክሌት ተስማሚ የሆኑ ከተሞችን ደረጃዎች ቢመሩም የካናዳዋ ሞንትሪያልም ብትሆን በብስክሌት መሰረተልማት በዓለም አቀፋዊ ደረጃ መሪነቱን ትይዛለች።
ከተማዋ ባለፉት አመታት 600 ኪሎ ሜትር የብስክሌት መንገዶችን በሰፋፊ ጎዳናዎቿ ላይ በመጨመር የብስክሌት መሠረተ ልማቷን ለማሻሻል ኢንቨስት አድርጋለች።
ከተማዋ በየአመቱ የብስክሌት ፌስቲቫል የምታስተናግድ ሲሆን ይህም ብስክሌተኞች ከተማዋን እንዲዞሩ ያስችላቸዋል።
5/ስትራስቦርግ ፈረንሳይ
ከተማዋ የተማከለ የከተማ የብስክሌት ኔትወርክ አዘጋጅታለች፡፡
በዚህም ምክንያት በፈረንሳይ የመጀመሪያዋ የብስክሌት ከተማ ተደርጋ ትቆጠራለች።
ከተማዋ ከጥቂት አመታት በፊት የነበረውን የመጓጓዣ አውታር በማደስ አዲስ አሽከርካሪዎች ከመኪኖች ይልቅ ብስክሌታቸውን እንዲያሽከረክሩ የሚያበረታታ ስትራቴጂ ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች።
ከዚህም ባሻገር ስትራስቦርግ የብስክሌት አውራ ጎዳናዎችን በማስፋፋት የጭነት ብስክሌቶችን ለመጠቀም እንቅስቃሴ ጀምራለች፡፡
በሀገራችንም በተለይ በአዲስ አበባ አዳዲስ እየተሰሩ ባሉ መንገዶች ላይ የሳይክል አሽከርካሪዎችን ከግምት ያስገባ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ መመለክት ቢቻልም ግን ከከተማዋ ስፋትና የመኪና መጨናነቅ ጋር ሲነጻጸር ግን እጅግ አናሳ የሚባል ነው፡፡
በአክረም ኑረያ
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት