አዲስ አበባ |የካቲት 08 2015 | NBC ETHIOPIA-ዛሬ በተጀመረው 42ኛው የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈጻሚዎች ስብሰባ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አድርገዋል።

በንግግራቸውም የአፍሪካ አገራትና የአፍሪካ ኅብረት እንዲሁም አጋር አካላት በኢትዮጵያ በዘላቂነት ግጭት ለማቆም ለተደረሰው ሥምምነት ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በነበረችበት አጋጣሚ በብዙ መድረኮች ከጎኗ በመቆም አጋርነታቸውን ላሳዩ አፍሪካዊያንም ምስጋና አቅርበዋል።
በተለይም ደግሞ አንዳንድ አካላት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ሲያሳድሩ በባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ ጭምር አፍሪካዊያን ከኢትዮጵያ ጋር በመሰለፍ አጋርነታቸውን ማሳየታቸውን አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ ባሳለፈቻቸው የፈተና ጊዜያት ከአፍሪካ ኅብረትና ከአፍሪካዊያን ያገኘነው ድጋፍ አኩርቶናል፤ በአፍሪካ ላይ ያለንን እምነትም እጅጉን አጠናክሮታል ብለዋል።
በመንግሥትና በሕወሓት መካከል የተደረሰው የሠላም ሥምምነት “ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ መስጠት የሚለውን የኅብረቱ ቁልፍ መርህ ገቢራዊ በማድረግ ትልቅ ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የሠላም ሥምምነቱ አሁን ላይ በተለያዩ የትግበራ ደረጃ ላይ መሆኑን ጠቁመው የሰብዓዊ ድጋፍ በማቅረብ በግጭቱ የተቋረጡ አገልግሎቶችን መልሶ በማስጀመር አመርቂ ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቅሰዋል።
ጎን ለጎንም ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በመሆን የሠላም ሂደቱ የአፈጻጸም ትግበራ በመልካም ደረጃ ላይ መሆኑን ገልጸው በተለይም ትጥቅ በመፍታትና ወደ ማኅበረሰቡ በመቀላቀል አበረታች ውጤት እየተገኘ ነው ብለዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ተቋም ጋር በጋራ ያደረጉትን ጥናት ተከትሎ ያቀረቡትን ምክረ-ሃሳብ በመቀበል እየተገበረች ነው ብለዋል።
በተለይም ደግሞ ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚኒስትሮች የጋራ ግብረ-ሃይል በማቋቋም እየሰራች መሆኑን ገልጸው እንዲያም ሆኖ የተ.መ.ድ የሰብዓዊ ተቋም ይህንን የኢትዮጵያ ጥረት ወደ ጎን ማለቱ ተቀባይነት እንደሌለው ነው ያስረዱት።
የአፍሪካ የሰብዓዊና የሰዎች መብት ኮሚሽን በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማጣራት የተናጠል ቡድን ማቋቋሙ ኢትዮጵያ የተመድ አቻ ተቋም ጋር በመሆን የምታካሂደውን ጥረት የሚያቃልል ነውም ብለዋል። ያም ብቻ ሳይሆን በጋራ ጥናት ይካሄድ የሚለውን የኢትዮጵያን ጥያቄ ውድቅ ያደረገ መሆኑን ጠቁመው በሠላም ሥምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ በሽግግር ፍትህ ላይ ብሔራዊ ምክክር እያደረገች ያለውን ጥረትም ያላገናዘበ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም አፍሪካዊያን አስካሁን የሚያደርጉትን አጋርነት አሁንም በድጋሚ እንዲያሳዩ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ ፓን አፍሪካኒዝም ለአፍሪካ አንድነትና ምጣኔ ሃብታዊ አድገት ወሳኝ ነው ብላ ታምናለች ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፤ በተለይም በአፍሪካ የጥይት ድምጽ እንዳይሰማ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት አፍሪካዊያን በባለቤትነት መምራት አለባቸው ብለዋል።
በመሆኑም የአፍሪካ ኅብረት በአህጉሪቱ ፓን አፍሪከኒዝምን ለማጠናከር የሚያስችል ዓመታዊ የወጣት መሪዎች ጉባኤ ጉባኤ ሊኖረው እንደሚገባ ገልፀው፡፡ ይህም የወደፊት የአፍሪካ ኅብረት ሥራዎችን ከወጣቶች ጋር ለማሰናሰልና የፓን አፍሪካኒዝም መርሆዎችን ለማስቀጠል ያስችላል ብለዋል።
ወጣቶች የሚሰሯቸው ሥራዎች በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር እንዲካሄድና የአፍሪካ አንድነት እንዲሁም ምጣኔ ሃብታዊ አድገት እንዲኖር ያስችላል ነው ያሉት።
ሃና ተሰማ
ምንጭ (ኢዜአ)
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት