፨ ፨ ፨ ፨ ፨፨ ፨ ፨ ፨ ፨
ከዛሬ 79 ዓመት በፊት በጎርጎሮሳውያኑ ሐምሌ 30፣1945 የጃፓኖቹ ሁለት ከተሞች ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ ዱብዳ ወረደባቸው፡፡ ከተሞቹ በአሜሪካ አቶሚክ ቦንብ ጋዩ፡፡ በቅጽበት የበርካታ ጃፓናዊያን ህይወት ውጥንቅጡ ወጣ፡፡
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወደመጠናቀቁ እያመራ ባለበት ወቅት ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ፣ ቻይና እና ሶቪየት ህብረት አባል የሆኑበት ጥምረት የጃፓንን ዋና መሬት ለመውረር ዝግጅት ማድረግ ጀመረ፡፡
የፓስፊክ ጦርነት በጃፓን ኢምፓየር እና አራቱ ሀገራት በመሰረቱት ጥምረት መካከል የተደረገ ጦርነት ነው፡፡ እስያ-ፓስፊክ ጦርነት እና የፓስፊክ ቲያትር በሚል ስያሜም ይታወቃል፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በምስራቅ እስያ፣ በፓስፊክ ውቅያኖስ፣ በሕንድ ውቅያኖስ እና በኦሺያኒያ የተካሔደ ጦርነት ነው፡፡ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተካሄደባቸው አካባቢዎች አብዛኛውን ስፍራ የያዘ ስለመሆኑ ይነገርለታል፡፡
በሁለት ምዕራፍ ተከፋፍሎ ጃፓንን ለመቀራመት እቅድ ተያዘ፡፡ ከጃፓን አራት ዋና ዋና ደሴቶች መካከል በትልቀቱ ሶስተኛ የሆነውን የኪውሹ ደሴት አሜሪካ በብቸኝነት ልትይዘው፣ ከሌሎቹ የጥምረቱ አባላት ጋ በመሆን ደግሞ ከመዲናዋ ቶኪዮ አቅራቢያ የሚገኘውን እና ካንቶ የተሰኘውን የሀገሪቱን ሰፊ ቦታ ለመቆጣጠር እቅድ ተሰርቶ አለቀ፡፡
የጥምረቱ የጥቃት ዝግጅት ተገማች ስለነበር ጃፓንም ዝግጅት ማድረግ ጀመረች፡፡ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ገደማ የሀገሪቱ ጦር ሠራዊት 28 ሚሊዮን ከሚሆኑ ለሀገራቸው በፈቃዳቸው ለመዋጋት ከወሰኑ ሲቪል ሚሊሻዎች ጋር በህብረት እናት ሀገራቸውን ለመከላከል በተጠንቀቅ ቆሙ፡፡
የእነ አሜሪካው ጥምረት ደግሞ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ባደረገው ጥናት ከ1 ነጥብ 7 እስከ 4 ሚሊዮን የሚገመት ጉዳት እንደሚያጋጥም እንደሚችል ቅድመ ግምት ተቀምጦ ወደ ጦርነቱ ተገባ፡፡ ከእዚህ መካከል 800 ሺህ የሚደርሰው ሞት ነበር፡፡ ከጃፓን በኩልም ከአምስት እስከ 10 ሚልዮን ሞት እንደሚኖር ትንበያ ተቀምጧል፡፡ 20 ሚሊዮን የሰው ሃይሏን እንደሚነጥቃት ግምት ያስቀመጠችው ጃፓን ዝግጅቷን ለሚቃጣባት ጥቃት ይመጥናል ባለችው ልክ ተሰናዳች፡፡
በቴክኒክ ችግር፣ በመጥፎ የአየር ሁኔታ እና በጠላት የጃፓን ጦር አልረታም ባይነት ሳቢያ ጥምረቱ ቀደም ሲል የያዘውን የጥቃት እቅድ ተደጋጋሚ ውድቀት አጋጠመው፡፡ ይህንም አዲስ ዕቅድ እንዲያወጣ የግድ አለው፡፡ በእዚህ መሰረትበሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የዓየር ጥቃቶች ይደረጉ ነበር፡፡ የዓየር ጥቃቶቹ ዋነኛ ዓላማ የጠላትን ኢንዱስትሪዎች የማውደም፣ የእነኚህን ኢንዱስትዎች ሰላማዊ ሰራተኞች መግደል አሊያም ከስራ ውጪ ማድረግ እንዲሁም የሲቪል ሰዎችን ስነ-ልቦና ማዳከም ነው፡፡
ይህ ስትራቴጂያዊ የቦምብ ጥቃት በብዛት ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ በእዚህ መንገድ ጃፓንን በቦምብ ለማደባየት እቅድ ተነደፈ፡፡ በእቅዱ መሰረት በቀጣዮቹ ስድስት ወራት 64 የጃፓን ከተሞች በእሳት ወደሙ፡፡ የጃፓን ጦር ጥቃቱን ሊቋቋመው አልቻለም፡፡ ሃይሉን እያጣ መጣ፡፡

የባሰው አስከፊ ቀን ግን ገና ነበር፡፡ የሟች አሜሪካውያንን ቁጥር ለመቀነስ በሚል አሜሪካ በጦር መኮንኗ እና ፖለቲከኛው ጆርጅ ማርሻል አማካኝነት አንዳች የጦር መሳሪያ ለመጠቀም ማሰብ ጀመረች፡፡ መርዛማ ጋዝን እንደ ጦር መሳሪያ፡፡ ብዛት ያላቸው የተለያየ ዓይነት መርዛማ ጋዞች ከክምችት ወጥተው ለጦርነቱ ተዘጋጁ፡፡
የኬሚካል፣ የራዲዮሎጂ እና የኑክሌር ጦር መሣሪያዎችን የመከላከልና የመጠቀም ኃላፊነት የተሰጠው የአሜሪካ ጦር አካል የመርዛማ ጋዞቹ አጠቃቀም ላይ ስልጠና እንዲወስዱ ተደረገ፡፡
በስተመጨረሻም የመርዛማው ጋዝ ጥቃት የሚደረግባቸው አምስት ከተሞች እንዲለዩ ተደረገ፡፡ በእዚህ መሰረት የአሁኗ ኪታኪውሹ የያኔዋ ኮኩራ፤ የጃፓን ወታደራዊ ሃይል ዋና መሥሪያ ቤት መቀመጫ የነበረችውና የኢንዱስትሪ ማዕከሏ ሂሮሺማ፤ የአውሮፕላን የተለያዩ ማሽኖች፣ የኤሌክትሪክ መሣሪያዎች እና የነዳጅ ማጣሪያዎች ማምረቻ የሆነችው ዮኮሃማ፤ የነዳጅ ማጣሪያ፤ ብረታ ብረትና አልሙኒየምን ጨምሮ የኢንዱስትሪ ተቋማት እና የወደብ መገኛ የሆነችው ኒገታ፤ እና ዋነኛ የኢንዱስትሪ ማዕከል የሆነችው ኪዮቶ በተለያዩ መመዘኛዎች የጥቃቱ ኢላማ እንዲሆኑ ተመረጡ፡፡ ኋላ ላይ በኪዮቶ ምትክ ናጋሳኪ እንድትተካ ተደረገ፡፡

በጎርጎሮሳውያኑ ሐምሌ 30፣1945 የጃፓኖኗ ከተማ ሂሮሺማ ከየት መጣ ያልተባለ ዱብዳ ወረደባት፡፡ ከተማዋ በአቶሚክ ቦንብ ድብልቅልቋ ወጣ፡፡ ከሶስት ቀናት በኋላ ናጋሳኪም ተመሳሳይ እጣ ፋንታ ደረሳት፡፡ በእዚህ አሰቃቂ እልቂት በሁለቱ ከተሞች ብቻ የተረጋገጠ ባይሆንም የሟቾች ቁጥር ከ150 ሺህ እስከ 246 ሺህ እንደሚደርስ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ቁጥሩ ከፍንዳታዉ በኋላ በህይወት ተርፈው በአቶሚክ ቦንቡ መርዛማ ጨረር ተመርዘው የሞቱትን ያካትታል፡፡
የኒኩሌር ቦምቡ ከወደቀበት ከዋናዉ ቦታ ርቀው የሚገኙት ብቻ በህይወት መትረፍ ቻሉ፡፡ በተዓምር ከሞት ያመለጡትም ፊት እና ሰውነታቸው ተላልጦ ማንነታቸውን መለየት አዳጋች ሆኖ ነበር፡፡ በጨረሩ ተመርዘዉ ለተለያዩ በሽታዎች የተዳረጉትን ቤት ይቁጠራቸው፡፡
ከጥቃቱ ሰለባዎች መካከል አብዛኞቹ ንጹሃን ነበሩ፡፡ በርካታ ህጻናት ያለወላጅ ቀሩ፣ ጃፓናውያን ወላጆች አድገው ይጦሩኛል ያሏቸውን የዓይን ማረፊያ ልጆቻቸውን ተነጠቁ፡፡ ጃፓን የምድር ሲኦል ሆነች፡፡ ክስተቱ በዓለም ታሪክ የኒውክለር ጦር በጦርነት ጥቅም ላይ የዋለበት የመጀመሪያው ክስተት ሆኖ በታሪክ ሰፍሯል፡፡
ዛሬም ድረስ ሲታወስ ጃፓናውያን የቆየ ግን የማይድን ቁስላቸውን እያመረቀዝ ፊታቸውን በእንባ የሚያጥበው፣ ለተቀረው የዓለም ህዝብ ለመስማት የሚሰቀጥጥ አሰቃቂውን ጅምላ ጨራሽ ጥቃት የተፈጸመበትን የመጀመሪያው ቀን ሐምሌ 30፣1945ን ከታሪክ ማህደር መዘን አስታወሳናችሁ፡፡
በ-መቅደስ ደምስ












