፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ግንቦት 19 2016| NBC ETHIOPIA- የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጋር ተወያይተዋል።
በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ተስፋሁን ዓለምነህ አዲስ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሰፋ የፖለቲካ ፓርቲዎች መቃወም ላይ መሠረት ካደረገ እንቅስቃሴ በመላቀቅ በተፎካካሪነት ውስጥ በትብብር ለሀገር መሥራት እንዲችሉ ታሳቢ ተደርጎ የጋራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት መመስረቱን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መተማመን እና ሰላምን መሠረት ያደረገ ግንኙነት እንዲኖር የጋራ ምክር ቤቱ መመሥረቱን ገልጸዋል። ችግሮችን በጋራ ለመፍታት መተማመን እና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲኖር የጋራ ምክር ቤቱ ማስፈለጉን አንስተዋል።
በተለያየ የፖለቲካ አቋም ውስጥ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ውይይት ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑንም አመላክተዋል። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የእርስ በእርስ ግጭት ትልቅ ቦታ ያለው በመሆኑና ችግሩን ለመፍታት የሠለጠነ ሰላማዊ የፖለቲካ ትብብር አስፈላጊ በመሆኑ የጋራ ምክር ቤት ማቋቋም ማስፈለጉን ገልጸዋል። የጋራ ሀገር እና የጋራ ሕዝብ እስካለ ድረስ በትብብር መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት።
የጋራ ምክር ቤቱ ምርጫ በሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ፣ በተለያየ ጊዜ የሃሳብ ልዩነቶች ወደ ግጭት እንዳያመሩ ምክረ ሃሳቦችን በማቅረብ፣ በሕልውና ጦርነቱ ጊዜ የጋራ ምክር ቤቱ በጋራ በመወሰን የማይተካ ሚና ተጫውቷል ነው ያሉት።
በህብረተሰቡ ውስጥ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱም ገልጸዋል። ለሰላም ግንባታ እና መረጋጋት ውይይት እና ድርድርን ማስፋት ይገባል ብለዋል። አለመግባባቶችን ለመፍታት ሰላማዊ ውይይቶችን ማድረግ ይገባልም ብለዋል።
የፖለቲካ ጥያቄ አለኝ የሚል አካል ውይይትን መቀበል አለበት ነው ያሉት። የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገር ማሰብ እና ለሀገር መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አንስተዋል። መንግሥት ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ ፓርቲዎችም ተጠያቂነት አለ ነው ያሉት። የፖለቲካ ፓርቲዎች መቻቻል እና ብዝኃነትን ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። ብዝኃነትን እና መቻቻል አስፈላጊ ጉዳይ ነው ያሉት ሠብሣቢው መቻቻል እና ብዝኃነት ላይ መሥራት ካልተቻለ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ አይቻልም ነው ያሉት። የፖለቲካ ፓርቲዎች ለማኅበራዊ ፍትሕ መሟገት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል። ፖለቲካ አቅም፣ አቋም እና ተሻጋሪነትን ይጠይቃልም ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ የሚመክሩበት አውድ በኢትዮጵያ ብዙ የተለመደ እንዳልነበር አንስተዋል። ችግሮችን በውይይት ከመፍታት ይልቅ ሌሎች አማራጮችን የመጠቀም ልምድ እንደነበርም ገልጸዋል። አሁን የተፈጠረው አውድ እና ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሚደረጉ ውይይቶች የሚደነቁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
“የአማራን ሕዝብ መብት እና ጥቅም ማስከበር የጋራ አጀንዳችን ነው” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የአማራ ክልልን ሉዓላዊነት ማስከበር ሌላው የጋራ አጀንዳ መሆኑንም ገልጸዋል። አብረን ለመሥራት የሚያስገድዱን ጉዳዮች አሉም ብለዋል። በጋራ የሚደረጉ ውይይቶች ወሳኝ መሆናቸውንም አንስተዋል።
የፓርቲ ለፓርቲ፣ የፓርቲ እና የመንግሥት፣ የፓርቲ እና የሕዝብ ውይይቶች እንደሚያስፈልጉም ገልጸዋል። “በጋራ ሥንሠራ የክልሉን መብት እና ጥቅም እናስከብራለን፣ ከአደጋ እንጠብቀዋለን” ነው ያሉት። ሃቅ ላይ የተመሠረተ ውይይት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Website – https://nbcethiopia.com/news/
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv

See insights and ads
All reactions:
11












