፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሚያዚያ 01፣ 2016| NBC ETHIOPIA-በአለማችን አቬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ግዙፉ የአውሮፕላን አምራች የሆነው ቦይንግ ኩባንያ ባለፉት አመታት አምርቶ ለገበያ በሚያቀርባቸው የተለያየ አይነት እና መጠን ባላቸው አውሮፕላኖቹ፤ ከጥራት ጋር ተያይዞ ቅሬታዎች ሲነሱበት ቆይቷል፡፡
የኩባንያው ምርት የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ላይ በተደጋጋሚ አደጋዎች እየተከቱ መምጣጡን ተከትሎ ከምርት ጥራትና ደህንነት ጋር ተያይዞ በሃገራት ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬን አሳድሯል፡፡ ከህግ አውጭዎች እና ተቆጣጣሪ አካላትም ቢሆን ጫና ሲበረታበት ቆይታል፡፡
ንብረትነቱ የአሜሪካው የሳውዝዌስት አየር መንገድ የሆነው ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን እሁድ እለት በበረራ ወቅት የሞተሩ ሽፋን ተገንጥሎ መውደቁ ተሰምቷል፡፡
የሳውዝዌስት አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737 -800 የበረራ ቁጥር 3695 135 ተሳፋሪዎች እና 6 የበረራ ሰራተኞችን በማሳፈር ወደ ሂዩስተን ሆቢ አውሮፕላን ማረፊያ በሚያቀናበት ወቅት አደጋ እንደደረሰበት ነው የተገላፀው፡፡
አውሮፕላኑ በ10,300 ጫማ (3,140 ሜትር) ከፍታ ላይ ሲበር በነበረበት ወቅት ባጋጠመው የሞተር ሽፋን መገንጠል ተከትሎ አውሮፕላኑ በዴንቨር ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ መገደዱን አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግባዋል፡፡ አውሮፕላኑ ተጨማሪ ችግር ሳይከሰትበት አንዲሁም ተሳፋሪዎች ላይ ምንም ጉዳት ሳይደርስ በሰላም ማረፉ ተነግሯል፡፡ ሳውዝዌስት አውሮፕላን ተሳፋሪዎቹን ከሦስት ሰዓታት መዘግየት በኋላ በሌላ አውሮፕላን ወደ መዳረሻቸው መጓዛቸውን አስታውቋል።

ቦይንግ ያገጠመውን የሞተር ሽፋን መገንጠል አደጋ ተከትሎ የአሜሪካ አየር መንገድ ተቆጣጣሪ የሆነው የፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር በቦይንግ አውሮፕላን ላይ ዳግም ምርመራ ማድረግ መጀመሩን አስታውቃል፡፡
በቦይንግ 737-800 አውሮፕላን ላይ የተፈጠረው ክስተት ግዙፉ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ላይ የደህንነት ጥያቄ እየተነሳበት ባለበት ወቅት መሆኑም ጉዳዩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም ቦይንግ ተጨማሪ ጫና ውስጥ ገብቷል ነው የተባለው።
አየር መንገዱ በተፈጠረው ክስተት ደንበኞች ላጋጠማቸው መጉላላት ይቅርታ ጠይቆ፣ ቅድሚያ የደንበኞች እና ሠራተኞችን ደኅንነት ማረጋገጥ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው ብሏል፡፡
እንዲሁም አየር መንገዱ በሰጠው መግለጫ እንዲህ ያሉትን ክፍሎች የመቆጣጠር ብሎም የመፈተሸ ኃላፊነት እንዳለበት ያረጋገጠ ሲሆን የአየር መንገዱ የጥገና ቡድን ባለሙያዎችም በአውሮፕላን ያጋጠመውን ክስተት መነሻ መንስኤውን እየገመገመ መሆኑን ተናግሯል።
ተገንጥሎ የወደቀው የሞተር መሸፈኛ በአየር መንገዱ ባለሙያዎች የሚጠገን የአውሮፕላን አካል መሆኑን አየር መንገዱ አረጋግጦ የሞተር መሸፈኛው እንዴት ተገንጥሎ ሊወድቅ እንደቻለ ምርመራ ጀምሬያለሁ ብሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አየር መንገዱ በአውሮፕላኑ ሞተር ለመጨረሻ ጊዜ ጥገና ያደረገው መቼ እንደሆነ ለመናገር ፈቃደኛ አለመሆኑን ሲ ኤን ኤን አስነብባል፡፡ እንዲሁም ቦይንግ ኩባንያም በሳውዝዌስት አየር መንገድ አውሮፕላን እና የበረራ እንቅስቃሴ መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆኑን ቢቢሲ በቢዝነስ አምዱ አትቷል፡፡
የቦይንግ 737-800 አውሮፕላን እ.ኤ.አ በ2015 መመረቱን የአሜሪካ የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር መረጃ ያመላታል፡፡ ቦይንግ ሰራሹ 737-800 አውሮፕላን ብዙ የደኅንነት ጥያቄ እየተነሳበት ያለው የቦይንግ 373-800 ማክስ አውሮፕላን የቀደመ ስሪት መሆኑም ተገልፃል፡፡ የእነዚህ ሁለት አውሮፕላኖች የሞተር ክፍል በጄኔራል ኤሌክትሪክ ኤሮስፔስ እና በሳፍራን ኤየርክራፍት ኢንጂንስ ኩባንያዎች ጥምረት የሚመረተው ሲኤፍኤም56 የተሰኘ ሞተር ነው የተገጠመላቸው።
ግዙፉ የአውሮፕላን አምራች ቦይንግ ኩባንያ በቦይንግ አውሮፕላኖች ላይ ከዚ ቀደም በተደጋጋሚ አደጋ እያጋጠመው ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞም በምርቶቹ የደኅንነት ደረጃ ላይ ጥያቄ እያስነሳበት ይገኛል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም ኩባንው በተደጋጋሚ በሚነሳበት የምርት ጥራት ችግር ላይ ጥናት ሲያደርግ መቆየቱን በተከታታይ ሲገልጽ ነበር፡፡ ከግምገማውም በኃላ ቦይንግ 50 737 ማክስ አውሮፕላኖች ላይ ተጨማሪ የደህንነት ስራዎችን መስራት እንደሚገባ ያጠናው ጥናት ማመላከቱንም ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡
ባሳለፍነው ጥር የአላስካ አየር መንገድ ላይ በደረሰው የመስኮት መንገጠል ችግር ምክንያት በአውሮፕላኑ ክፍል በተለያዩ አካላት ላይ ክትትል ሲደረግበት ቆይቷል።
በሳለፍነው ሳምንትም ቦይንግ የአላስካ አየር መንገድ ላጋጠመው ኪሳራ
160 ሚሊዮን ዶላር ካሳ መክፈሉ ይታወሳል፡፡ ከአላስካ አውሮፕላን ላይ በደረሰው የመስኮት መገንጠል ተከትሎ 200 የሚጠጉ ቦይንግ 737 ማክስ 9 አውሮፕላኖችን ለጊዜው ከበራራ ታግደው ቆይተዋል፡፡
ቦይንግ ሠራሹ 737 ማክስ አውሮፕላን ከበረራ መቆጣጠሪያ ችግር ጋር በተያያዘ የኢንዶኔዢያ እና የኢትዮጵያ አየር መንገዶች አውሮፕላኖች ከተከሰከሱ በኋላ አውሮፕላኑ በመላው ዓለም ለ20 ወራት ከበረራ ታግዶ ቆይቷል።
እ.ኤ.አ. በ2018 እና 2019 በ737 ማክስ አይሮፕላን ላይ በተከሰተ አደጋ ቦይንግ ለረጅም ጊዜ የገነባው ስሙን ለመጠገን ለዓመታት ሲጥር ተስተውሏል፡፡
????YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
???? TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
????Website – https://nbcethiopia.com/news/
????Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት












