
የኢትዮጵያ እዳ ከከፍተኛ ተጋላጭነት ወደ መካከለኛ ደረጃ ዝቅ ማለቱ የሪፎርሙ ትልቁ ስኬት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን በማካሄድ ላይ ይገኛል።
በመደበኛ ጉባኤው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ መስከረም 26 ቀን 2019 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ስብሰባ ያቀረቡትን የ2019 ዓ.ም የመንግሥት ዕቅድ መነሻ በማድረግ የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄና አስተያየቶቻቸውን አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለቀረቡ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሪፎርሙ ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ እዳ ጫና መቀነስ እና ጤናማ ማድረግ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።
በሪፎርሙ የኢትዮጵያን የእዳ ተጋላጭነት ወደ መካከለኛ ዝቅ ለማድረግ ሲሰራ መቆየቱን አመልክተዋል።
በዚህም ከታቀደው ጊዜ ቀድሞ የኢትዮጵያ እዳ ሁኔታ ወደ መካከለኛ ደረጃ ዝቅ ማለቱንና ይህም የሪፎርሙ ትልቅ ስኬት መሆኑን አመልክተዋል።
የመንግሥት ልማት ድርጅቶች እና ተቋማት ከብክነት ወጥተው ወደ ትርፋማነት መሸጋገራቸው ለተገኘው ውጤት አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቅሰዋል።











