በኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓቱ በብቁ የሰው ሃይል፣ በጠንካራ ተቋማት፣በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በተደራጀ አሰራር እየተገነባ እንደሚገኝ የፌዴራል ሕግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ ገለፁ።
በኢትዮጵያ የዳኝነት የሕግ ማዕቀፍ እና አተገባበር በሚል ርዕስ ኢንስቲትዩቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት ሲምፖዚየም እያካሄደ ነው።
የፌዴራል ሕግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ በሲምፖዚየሙ ላይ እንደገለጹት፤ የዳኝነት ስርዓት በማህበረሰብ ውስጥ ጽኑ መሰረት ያለው የሕገ መንግሥታዊነትና የሰብዓዊ ክብር ዋስትና ነው።
የፍትህ ስርዓቱ በዳኞች ብቻ ሳይሆን በጠንካራ ተቋማት፣ በብቁ የሰው ሃይል፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና በተደራጀ አሰራር እየተገነባ መሆኑን ገልፀዋል።
ዳኞች ሕግን የሚተረጎሙ ብቻ ሳይሆን በህብረተሰቡ ዘንድ መተማመን የሚጠብቁና ፍትህን በጽናት የሚያቆሙ ምስሶዎች ናቸው ብለዋል።
የሕግ የበላይነትን ለማስጠበቅ ህብረተሰቡ በሕግ ሥርዓቱ ላይ እምነት እንዲኖረው እና የፍትህ ስርዓቱን ለማዘመን የዳኝነት ደህንነት የህግና አሰራር ስርዓት ማጠናከር እንደሚገባም ገልፀዋል።
በዚህም ኢንስቲትዩቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የህግ ምሁራን፣ የፖሊሲ አውጪዎችን እና የፍትህ ተቋማት መሪዎችን በአንድ ላይ በማሰባሰብ የዳኞችና የፍትህ ተቋማት ደህንነት ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የዳኝነት አሰራርን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ማድረግ የመረጃ ስርዓትን ለማዘመን እና የስራ ጫናን ስለሚቀንስ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።














