
አዲስ አበባ ከተማ መጪውን ትውልድ ጭምር ታሳቢ ባደረገ መልኩ እየተገነባች መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በናይጀሪያ ምክትል ፕሬዚዳንት ካሺም ሸቲማ ከተመራ ልዑክ ጋር በሕፃናት እድገትና በከተማ ልማት ዙሪያ የልምድ ልውውጥ አድርገዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በመዲናዋ በመንገድ፣ በቤቶች፣ በትራንስፖርት፣ በወንዝ ዳርቻዎች፣ በፓርኮች እና በዲጂታል አገልግሎቶችና በሌሎችም ሰፊ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል።
የከተማዋ ዕድገት የሰዎችን ሕይወት የሚቀይር መሆኑንም አንስተዋል።
ከተማዋ የዛሬን ፍላጎት ብቻ ሳይሆን መጪውን ትውልድ ጭምር ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ እየተገነባች መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
አዲስ አበባን ለሕፃናት ምቹ ለማድረግ ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸውን እና የመጫወቻ ሜዳዎችና የማቆያ ማዕከላት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን አመላክተዋል።
የትምህርት ቤት ምገባ፣ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ተደራሽነትን ማስፋፋትና በሕፃናት እድገት ላይ ድጋፍ ማድረግ ለቀጣይ ትውልድ የሚደረግ ትልቅ ኢንቨስትመንት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በአሁኑ ወቅት በመዲናዋ የልጆች ወደ ትምህርት ቤት የመሄድ ምጣኔና የተማሪዎች ትምህርት የመቀበል አቅም በእጅጉ እያደገ መምጣቱን አስረድተዋል።












