ዘ ኤንጅል (ሰሜን ለንደን ለዘላለም!)

የአርሰናል እግር ኳስ ክለብ ይፋዊ የጨዋታ መጀመሪያ መዝሙር የሆነው “ዘ ኤንጄል (ኖርዝ ለንደን ፎሬቨር)” ከአንድ መኝታ ቤት ውስጥ ከተቀረጸ ሙዚቃ ተነስቶ፥ ክለቡ የሻምፒዮናነትን ክብር እስከቀዳጀበት ታሪካዊ ዘመን ድረስ ያለውን ጉዞ እንዲያጠናቅቅ ረድቶታል።
ዕድሜ ልኩን የክለቡ ደጋፊ በሆነው ሉዊስ ደንፎርድ የተጻፈውና በለንደን ስለሚገኘው ኢስሊንግተን አውራጃ የሚተርከው ይሄው ስሜት ቀስቃሽ ዜማ፣ በአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ስር የክለቡ ዓለም አቀፋዊ የአንድነት ምልክት መዝሙር ለመሆን በቅቷል።
አርሰናል የ2025–26 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን በድል አድራጊነት ማንሳቱን ተከትሎ፥ ዘፈኑ በሙዚቃ ሰንጠረዦች ላይ በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ላይ በመውጣት በእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ስሙን በደመቀ ሁኔታ አስፍሯል።
እ.ኤ.አ. በ2021 መገባደጃ ላይ፥ በሰሜን ለንደን በሚገኘው መኝታ ቤቱ ውስጥ ተቀምጦ “ዘ ኤንጅል” ሙዚቃን የጻፈው አቀንቃኝ እና ገጣሚ ሉዊ ደንፎርድ ዘፈኑን ሲጽፍ በስታዲየም ውስጥ ይዘመራል ብሎ ፈጽሞ እንዳላሰበ ይናገራል።
በየካቲት 2022 “ዘ ፖፕሃም” (The Popham) የተሰኘው አነስተኛ አልበሙ አካል ሆኖ የተለቀቀው ይህ ትራክ፣ ለኢስሊንግተን እና ለአካባቢው ነዋሪዎችና ለደሀው ማህበረሰብ የተበረከተ ግላዊ የፍቅር ደብዳቤ ተደርጎ የተሰራ ነበር።
ሆኖም የዘፈኑ ግጥሞች የሰሜን ለንደንን ህይወት ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ በመሆናቸው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የአርሰናል ደጋፊዎችን ልብ መማረክ ቻሉ።
ደጋፊዎች በአንድ ኮንሰርት ላይ የዘፈኑን አዝማች በስሜት ሲዘምሩ የሚያሳየው ቪዲዮ በኢንተርኔት ላይ በሰፊው ከተሰራጨ በኋላ፣ የክለቡን ስነ-ልቦና መልሶ ለመገንባት በቁርጠኝነት ይሰራ የነበረውን የአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታን ትኩረት አግኝቷል።
ዘፈኑ ለመጀመሪያ ጊዜ በስታዲየም ውስጥ በይፋ የተደመጠው እ.ኤ.አ. በ2022 አርሰናል ሊድስ ዩናይትድን በጋበዘበት የጨዋታ ቀን ነበር። በወቅቱ በስታዲየሙ የነበሩ 60,000 ደጋፊዎችም በአንድ ላይ “ሰሜን ለንደን ለዘላለም፣ አየሩ ምንም ይሁን ምን፣ እነዚህ ጎዳናዎች የእኛ ናቸው…” እያሉ አዝማቹን በጋራ ዘምረዋል።
የዘፈኑ ተፅዕኖ ፈጣን ነበር። አርቴታ ከጨዋታው በኋላ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ዘፈኑ በተጫዋቾች ማረፊያ ክፍል ውስጥ በተጫዋቾቹ ላይ ምን ያህል ጥልቅ ስሜት እንደፈጠረ ተናግሮ፣ “ልዩ” እና “በጣም ስሜት የሚነካ” ተሞክሮ ሲል ገልጾታል።
ከዚያ ቀን ጀምሮ “ዘ ኤንጄል” የተለመዱትን የጨዋታ ዋዜማ ሙዚቃዎች በመተካት የአርሰናል ቋሚና የማይቀየር መዝሙር ከመሆን አልፎ አሁን ላይ አርሰናል በውድድሮች ላይ ካሳየው አስደናቂ ትንሳኤ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ሆኗል።
በሙዚቃው እና በክለቡ ስኬት መካከል ያለው ትስስር ፍፁም ጥንካሬውን ያገኘው አርሰናል ታሪካዊውን የ2025–26 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ካሸነፈ በኋላ ነው። ደጋፊዎች ክለቡ ከ2004 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘውን የሊግ ዋንጫ ለማክበር የለንደንን ጎዳናዎች ሲያጥለቀልቁ፣ “ዘ ኤንጄል” ዋነኛው የአሸናፊነት ማክበሪያ ዜማ ሆኖ አገልግሏል።
ይህ ከአራት ዓመታት በፊት የወጣው ትራክ በዩኬ አይቱንስ (UK iTunes) የነጠላ ዜማዎች ሰንጠረዥ ላይ እስከ ደረጃ 3 ድረስ መውጣት ችሏል። ሙዚቀኛው ሉዊ ደንፎርድም “ከአሁን በኋላ ይህ ዘፈን አይደለም፤ ታሪክ ነው” ሲል ስሜቱን አካፍሏል።
ልክ እንደ ሊቨርፑል “ዩ ዊል ኔቨር ዎክ አሎን” (You’ll Never Walk Alone) ሁሉ፣ አርሰናልም በመጨረሻ ሙሉ በሙሉ የራሱ የሆነ፣ ከአካባቢው ማህበረሰብ የፈለቀና ጥልቅ ስሜት ያለው መዝሙር አግኝቷል። በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ደጋፊዎች፣ “ዘ ኤንጄል” የሰሜን ለንደን ትክክለኛ መለያ ምልክት ሆኖ ይኖራል።
በ – ዳንኤል መኮንን












