
የኢትዮጵያ አየር ኃይል የተመሰረተበት 90ኛ ዓመት የምስረታ ቀን “የኢትዮጵያ አየር ኃይል የነፃነትና የአንድነት ምልክት” በሚል መሪ ቃል ከጥር 15/2018 ዓ/ም እስከ ጥር 19/2018 ዓ/ም በተለያዩ መርሃ ግብሮች እንደሚከበር ተገልጿል።
አየር ኃይሉ የተመሰረተበትን 90ኛ ዓመት የምስረታ ቀን ክብረ በዓል አስመልክቶ የሚኖሩ ሁነቶችን በተመለከተ ለጋዜጠኞች የገለጻ መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የ1ኛ አየር ምድብ አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል ብሩክ ሰይፉ ፥
ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚካሄደው ክብረ በዓል የሚያካትታቸውን ሁነቶች አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም በክብረ በዓሉ “የአንበሶች ሰማይ፤ ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል የተባበሩት አረብ ኢሚሬት፣ የሩስያ፣ የሞሮኮ እና የቼክ ሪፐብሊክ አየር ኃይሎች በጋራ 2ኛውን የጥቁር አንበሳ የአየር ትርዒት እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የወደፊቱን የአቪዬሽን አቅም በጋራ እንገንባ” በሚል መሪ ቃል የኢትዮጵያ አየር ኃይል እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ የአሜሪካ፣ የቻይና፣ የህንድ እና የደቡብ አፍሪካ ኩባንያዎች እንዲሁም በአቪዬሽን ዘርፍ የተሰማሩ ከ27 በላይ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት የአቬሽን ኤክስፖ እንደሚካሄድ ተመላክቷል።
”የጋራ ሥራዎቻችንን አጠናክረን የተረጋጋ ዓለም እንገንባ” በሚል መሪ ሀሳብም ከ38 በላይ የአፍሪካ ሀገራት የአየር ኃይል አዛዦች እና የዘርፉ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት የአፍሪካ አየር ኃይሎች ፎረም እንደሚካሄድም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ህብረተሰቡ በሚታደምበት መልኩ እንደሚከበርም ተመላክቷል።
በ-ሰላማዊት ወንድወሰን












