
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለ30 ሺህ የከተማዋ ዜጎች በተለይ ወጣቶች እና ሴቶችን ትኩረት ያደረገ የስራ ዕድል መፍጠሩን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
በከተማዋ ከሚከናወኑ የልማት ስራዎች ጎን ለጎን የነዋሪዎችን ኑሮ ለመሻሻል በሚሰሩ ስራዎች ስራ ዕድል ፈጠራ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዛሬው ዕለት የተካሄደው በአንድ ጀንበር ለ30 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል የመፍጠር ንቅናቄ የእዚሁ አካል መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡
የስራ ዕድሉ ተጠቃሚ ያደረጋቸው አዲስ ስራ ጀማሪዎቹ የስራ ዕድል ጥያቄ የነበራቸው መሆኑን ነው ከንቲበዋ የገለጹት፡፡
የስራ ዕድል ተጠቃሚዎቹ በኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው በከተማ ግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በንግድ፣ በአገልግሎትና በሌሎችም አዋጭ ዘርፎች ላይ በልዩ ሁኔታ በማሰማራት ስራ መጀመራቸውን ነው የተናገሩት፡፡
የሥራ ዕድል የተፈጠረላችሁ ዜጎች ከተማ አስተዳድሩ በሁሉም መስክ አስፈላጊዉን ድጋፍ እና ክትትል የሚያደርግላቸው መሆኑንም አስታውሰዋል።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክሕሎት ቢሮ ኃላፊ ሚሊዮን ማቲዎስ “የአንድ ጀምበር የሥራ ዕድል” የተለያዩ የስራ ዕድል ጥያቄ የነበራቸውን ዜጎች ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አዲስ አበባ በፈጣን እድገት እንደምትገኝ የጠቆሙት የቢሮ ኃላፊው ይህም የተገኘው በዜጎቿ ትጋት መሆኑ ገልጸዋል፡፡ በ2017 ዓ.ም ከ300 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስረ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት ለ350 ሺህ ዜጎች ቋሚ ስራ ዕድል ለመፍጠር እቅድ መያዙንና ባለፉት አራት ወራትም ከ158 ሺህ በላይ ወጣቶች ስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በየደረጃው ሲካሄዱ የቆዩት የሥራ ዕድል የመፍጠር ንቅናቄዎች መጠናቀቅን ተከትሎ፣ በመዲናዋ ለሚገኙ 30 ሺህ ወጣቶች በተለያዩ ዘርፎች “የአንድ ጀምበር የስራ ዕድል” ፈጠራ ንቅናቄ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ስታዲየም ተካሂዷል፡፡
በ-ሰላም ይልማ












