የሀዲያ የዘመን መለወጫ “ያሆዴ” በዓል በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች ታጅቦ በሀድይ ነፈራ እየተከበረ ነው፡፡
የሀድያ ደጃፍ(ሀድይ ነፈራ) ሃዲያዎች በጋራ በመሆን በዓሉን የሚያከብሩበት፣ የመረዳዳት የአብሮነት፣ የደስታ፣ የፍቅርና የመተጋገዝ ባህል በተግባር የሚታይበት ቦታ ነው፡፡ የሀዲያ የዘመን መለወጫ ያሆዴን ጨምሮ የተለያዩ ማህበራዊ ኩነቶችን በጋራ በሚከናወንበት በ “ሀድይ ነፈራ” በታላቅ ድምቀት በተለያዩ ሁነቶች ታጅቦ እየተከበረ ይገኛል፡፡

“ያሆዴ”ለሀዲያዎች የአዲስ ዘመን መለወጫና የተስፋ ብስራት ከመሆኑም ባለፈ ዘመድ ወዳጅ የሚሰባሰብበትና የሚመራረቅበት እንዲሁም ያለፈውን ዘመን የስራ ስኬት የሚገመግሙበት ለቀጣይ ስኬትም የሚመካከሩበት ነው፡፡
በያሆዴ በዓል በጋራ ይበላል፤ ይጠጣል፤ ከዚያም ለቀጣይ ስኬትና ብልጽግና የምርቃትና የእርድ እንዲሁም የደመራ ማቀጣጠል ስርዓት ይከናወንበታል፡፡
በአከባበሩ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) እና የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር)፣ እንዲሁም የክልሉ አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ስርሞሎ እና የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ ዲላሞ ኦቶሬ(ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ተጋባዥ እንግዶችና የአካባቢው ነዋሪዎች ታድመዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡












