:::::::::::::::::::::::::::::::::::::::
እስራኤል በታንክ በከፈተችው ተኩስ በደቡባዊ ካን ዮኒስ ከተማ ለእርዳታ ተሰልፈው የነበሩ 45 ፍልስጤማውያንን መግደሏን በጋዛ የሚገኘው የሃማስ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በጥቃቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መቁሰላቸው እና በርካቶች በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡የሟቾች ቁጥር አሁንም ሊጨምር ይችላል ተብሏል፡፡
የጤና ባለስልጣናት እንዳስታወቁት ትላንት በጋዛ ሰርጥ በስተደቡብ በሚገኙ የምግብ ማከፋፈያዎች አቅራቢያ በተፈፀመ የእስራኤል ጥቃት 34 ፍልስጤማውያን ሞተዋል፡፡
ጥቃቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በእስራኤል ወታደራዊ ቁጥጥር ስር ባሉ አካባቢዎች በጋዛ ሂውማኒትሪያን ፋውንዴሽን (GHF) ከሚመራው የእርዳታ ማዕከላት ምግብ ለማግኘት ሲጠባበቁ የደረሰ እና ከፍተኛው ሞት የተመዘገበበት ነው ተብሏል። ይህ ዜና እስከሚጠናቀርበት ሰዓት ድረስ እስራኤል ተፈፀመ ስለተባለው ጥቃት የሰጠችው ምላሽ የለም፡፡
በ-ሰላማዊት ወንድወሰን












