
የመደመር መንግሥት ለጠንካራና ገለልተኛ ተቋማት ግንባታ ከሰጠው ትኩረት አኳያ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከዓለም አቀፍ የብሔራዊ ሰብዓዊ መብት ተቋማት ጥምረት ያገኘውን ከፍተኛውን የደረጃ “A” ዕውቅና አስጠብቆ መቀጠሉን የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ በመገኘት ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፤ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በሁሉም መስክ እየፈካና እመርታዊ ለውጥ እያመጣ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም በዓለም አቀፍ የብሔራዊ ሰብዓዊ መብት ተቋማት ጥምረት (GANHRI) የ‘A’ ደረጃ ማግኘቱ የተቋማትን ግንባታ ስኬታማነት እንደሚያመለክት አስታውቀዋል።
ይህም ኢትዮጵያ በተቋማት ግንባታ፣ በአረንጓዴ ልማት፣ በከተማና ገጠር ኮሪደር፣ በኃይል ልማት፣ በኢንዱስትሪና በርካታ ጉዳዮች ምሳሌ እየሆነች መምጣቷን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ እንዳሉት፤ ኮሚሽኑ የዓለም አቀፉ የብሔራዊ ሰብዓዊ መብት ተቋማት ጥምረት (GANHRI) የ‘A’ ደረጃ ዕውቅና ያለው ተቋም ነው ብለዋል።
ይህ ደረጃ ተቋሙ በኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ በነጻነት አቋሙን የማሳወቅ፣ ጉዳዮችን የማንሳትና በዓለም አቀፍ መድረኮች የመሳተፍ ሰፊ ዕድል እንደሚሰጠው አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባለፉት አምስት ዓመታት የተቋማዊ ነጻነቱን በማጠናከርና በሰብዓዊ መብት ጥበቃ ረገድ ያለውን አቅም በማሳደግ ይህንኑ የ‘A’ ደረጃ ዕውቅና ማስጠበቁንም ገልጸዋል።
በቅርቡ በጄኔቫ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የብሔራዊ ሰብዓዊ መብት ተቋማት ጥምረት (GANHRI) ስብሰባም ኮሚሽኑን ጨምሮ የ14 አገራት ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋማት የደረጃ ግምገማ መከናወኑን አስታውሰዋል።
በዚህም የ‘A’ ደረጃቸውን የሚያስጠብቁ ተቋማት በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሥርዓት ውስጥ ጠንካራ ተቋማዊ ተሳትፎ እንደሚኖራቸው አብራርተዋል።
የ‘A’ ደረጃ ዕውቅናውን ማስጠበቅ ለኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ተደማጭነትን ከማስጨመሩም በላይ በዘርፉ የተቋማዊ መስፈርቶችን የሚያሟላ ብሔራዊ ተቋም እንዳላት የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአፍሪካ ደረጃም ኢሰመኮ በ46 አባል አገራት የተዋቀረውን የአፍሪካ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ትስስር (NANHRI) በምክትል ሊቀ መንበርነት እየመራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከአፍሪካውያኑ አባል አገራት 27ቱ ብቻ የ‘A’ ደረጃ ዕውቅና እንዳላቸው የጠቆሙት ዋና ኮሚሽነሩ፤ በቀጣናው የ‘A’ ደረጃ ዕውቅና ያላቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳና ቡሩንዲ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መንግሥት ያከናወናቸው የሪፎርም እርምጃዎችም በኮሚሽኑ የሕግና የአሠራር ማሻሻያዎች እንዲካሄዱ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
መንግሥት ተቋማዊ ነጻነት ላይ ጣልቃ ሳይገባ መቆየቱንና በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በሚከሰቱ ግጭቶች ላይ ኮሚሽኑ በመሄድ ገለልተኛ ምርመራና ክትትል እንዲያካሂድ ሰፊ ዕድል መሰጠቱንም አስረድተዋል።
ይህም ኮሚሽኑ በተቋማዊ ነጻነቱ በመመራት ሪፖርቶችን እንዲያወጣ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዲከታተልና ምርመራዎችን ለማካሄድ ያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግሥት የሚፈጸሙ ጥፋቶች በራሱ የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲገመገሙ ዕድል መፍጠሩም ለውጡን ያጠናከረ መሆኑን አክለዋል።
በዚህ የትብብር አሠራር ኢሰመኮ ከ799 በላይ እስረኞች እንዲፈቱ ማስቻሉን፣ በሰላም ግንባታ ሥራዎች መሳተፉንና ከጫካ የሚመጡ አካላትን በመቀበል የማስተናገድ ሥራ እያከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።
የ‘A’ ደረጃ ዕውቅናውን ማስጠበቅ ተቋማዊ አቅምና ነጻነት በማሳየት ኢትዮጵያ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት መድረኮች ያላትን ተሳትፎና ተደማጭነት ለማጠናከር የሚያግዝ መሆኑን አብራርተዋል።
ምንጭ፡ ኢዜአ









