ኢትዮጵያ የባህር በር የምትፈልገው ሌሎችን ለመጉዳት ወይም ለመቀማት ሳይሆን በጋራ ለማደግ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ።
7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ዛሬ የ1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ፤ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ የማደግ አስፈላጊነትን በማንሳት፣ ኢትዮጵያ ከኤርትራ መንግሥት ጋር በተለያዩ የልማት መስኮች አብሮ ለመሥራት ከፍተኛ ጥረት ማድረጓን ገልጸዋል።
በተለይም የኤሌክትሪክ መስመር በኢትዮጵያ ዋጋ የማስገባት እንዲሁም መንገድና ወደብ የመገንባት ሐሳቦች ቢቀርቡም አዎንታዊ ምላሽ አለመገኘቱን ጠቁመዋል።
በሰሜኑ ጦርነት ወቅት የኤርትራ መንግሥት ያሳየውን የመጀመሪያ የመልካም ጉርብትና ተግባር ያመሰገኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በቀጣይ ግጭቱ ወደ ትግራይ ሲሰፋ የተፈጸሙ ጥፋቶችና የፕሪቶሪያ ስምምነትን ተከትሎ የተፈጠረው ቅሬታ ችግር መፍጠሩን አብራርተዋል።
ከኤርትራ መንግሥት የሚጠበቁ ሁለት ዋና ዋና ነጥቦችን የለዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ የመጀመሪያው ለኢትዮጵያ ጠላቶች ማስታጠቂያና መተባበሪያ መሆን ማቆም ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በጋራ ልማት ላይ መሥራት መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለጋራ የልማት ሥራዎች ሐሳብ፣ ገንዘብና ጉልበት እንደምታዋጣ ገልጸው፤ ከዚህ ውጪ በኤርትራ ላይ ወረራ ለመፈፀም ዕቅድ እንደሌላትና ጉዳዩ በሰላምና በንግግር እንደሚፈታ አረጋግጠዋል።
የቀይ ባህር ጉዳይን በተመለከተም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሂቃን በተወሰኑ ጊዜያት የነበራቸውን የተሳሳተ ግንዛቤ አርመው ወደ ስትራቴጂካዊ ንቃት መምጣታቸውን ገልጸዋል።
የቀይ ባህር የዓለም ንግድ መስመርነት ከጥቂት ዓመታት በኋላ በአየር ንብረት ለውጥና በአዳዲስ የትራንስፖርት መስመሮች (እንደ አርክቲክ መስመር) ምክንያት ቀድሞ የነበረውን ጠቀሜታ ሊቀንስ እንደሚችል ጠቁመው፤ ይሁን እንጂ ለኢትዮጵያ የባህር በር አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር የምትፈልገው ሌሎችን ለመጉዳት ወይም ለመቀማት ሳይሆን፣ ጆርዳን ከሳውዲ ዓረቢያ ጋር፣ ኢራቅ እንዲሁም ፖላንድ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ያገኙትን ተሞክሮ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ በመተግበር በጋራ ለማደግ መሆኑን አብራርተዋል።









