ኢትዮጵያ እና ቻይና በኢትዮጵያ የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መስመር ተጨማሪ ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችል የድጋፍ ስምምነት ተፈራርመዋል።
በስምምነቱ መሠረት የባቡር መስመሩን ዘላቂነት፣ አስተማማኝነትና የሥራ ቅልጥፍና ለማሳደግ የሚውል የ15 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ይደረጋል፡፡
ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ትዕግስት ፍስሃ እና በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ከፍተኛ ዲፕሎማት ሊዩ ዚያኦጓንግ ፈርመዋል።
የገንዘብ ድጋፉ የኤሌክትሪክ ባቡሮችን ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችሉ አስፈላጊ መለዋወጫዎችን፣ የዋናውን መስመር ደህንነት የሚደግፉ የሐዲድና የጣቢያዎች ዕቃዎችን ያካትታል።
በተጨማሪም ለመደበኛ የሐዲድ ፍተሻና ጥገና የሚያገለግሉ አነስተኛ ማሽነሪዎች ይቀርባሉ፡፡
ይህ ስምምነት የኢትዮጵያ እና ቻይናን የጠበቀ የኢኮኖሚና የልማት አጋርነት የሚያሳይ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡




Source:
@NBCETHIOPIA
Via:
NBC Ethiopia












