የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ስብሰባ ቁ.8
ጥቅምት 24 ቀን 2019 ዓ.ም ፣ አዲስ አበባ ፣ ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ስምንተኛ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡ በተሻሻለው የባንኩ የማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1359/2025፣ አንቀጽ 23፣ በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መሠረት የተቋቋመው የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ በየጊዜዉ የገንዘብ ፖሊሲዎችን ነድፎ ለዳይሬክተሮች ቦርድ ምከረ-ሐሳቦችን በማቅረብ፣ ያስጸድቃል፡፡ በዚህ ረገድ፣ ኮሚቴው የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት፣የዋጋ ግሽበት፣ የበጀት፣ የውጭ ኢኮኖሚ፣ የገንዘብ አቅርቦትና የፋይናንስ ዘርፍ አዝማሚያዎችን፣ እንቅስቃሴ አመልካቾችን እንዲሁም በሀገር ውስጥ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ላይ ጉልህ አንደምታ ያላቸውን ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን ይገመግማል፡ ፡ ኮሚቴው ከእነዚህ የማክሮ ኢኮኖሚያዊ ግምገማዎችና የቅርብ ጊዜ የወደፊት ትንበያዎች በመነሣት በቦርዱ ፀድቆ ተግባራዊ የሚደረጉ የፖሊሲ ምክረ-ሐሳቦችን ያቀርባል፡፡
በዚሁ መሠረት፤ ኮሚቴው በውይይቱ ያካተታቸው ዐበይት ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው፡-
የዋጋ ግሽበት፡- ከአቅርቦት ችግር ጋር በተያየዘ ከፍ ብሎ የነበረዉ የዋጋ ግሽበት መቀነስ ያሳየ ቢሆንም በመስከረም ወር 2019 የታየዉ የ14.9 በመቶ ከብሔራዊ ባንክ የነጠላ አሃዝ የዋጋ ግሽበት ግብ አንጻር ከፍ ያለ መሆኑን ኮሚቴው ገምግሟል፡፡ የምግብ ዋጋ ግሽበት በሰኔ ወር 2018 ከተመዘገበው 15.1 በመቶ ወደ 14.8 በመቶ በመጠኑ የቀነሰ ሲሆን፣ ምግብ ነክ ያልሆነ የዋጋ ግሽበት ደግሞ ከ12.2 በመቶ ወደ 15.1 በመቶ ከፍ ብሏል። በምግብ ዋጋ ግሽበት ረገድ፣ የዳቦና የእህል ምርቶች፣ የአትክልትና ጥራጥሬ ምርቶች፣ እንዲሁም የቡና ዋጋ መጨመር ለዋጋ ግሽበቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ለምግብ ነክ ያልሆኑ ዕቃዎች ጭማሪ ደግሞ፣ በተለይም የኤሌክትሪክ ታሪፍ፣ የኬሮሲን እና የማገዶ እንጨት ዋጋ መጨመር ምክንያት ሆነዋል፡፡ በአጠቃላይ፣ በመስከረም ወር 2019 ለታየው የዋጋ ግሽበት በተለይ የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነትን ተከትሎ ዋነኛ ምክንያት ከአቅርቦት ጋር የተያያዘ መሆኑን መገንዘብ ተችሏል፡፡ የወደፊት የዋጋ ግሽበት አዝማሚያን በተመለከተ፣ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የትንበያ ጊዜ እየቀነሰ የሚሄድ ሆኖ ነገር ግን በድርብ አሃዝ ዉስጥ እንደሚቆይ ይገመታል፡፡
ዕድገትና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፡- ኮሚቴው የሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ ዕድገት ተጠናክሮ እንደቀጠለ ተገንዝቧል፡፡ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አመላካቾች በ2ዐ19 በጀት ዓመትም የተጠናከረ የኢኮኖሚ ዕድገት እንደሚኖር ያመላክታሉ፡፡ ለዚህም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በሲሚንቶ ምርት፣ በኤሌክትሪክ ማመንጨት እና በብረትና ብረታ ብረት ምርቶች ላይ የታዩ መሻሻሎች በአጠቃላይ የኢንዱስትሪ ዘርፉ ንቁ እንቅስቃሴ እንደሚኖረው ይጠቁማሉ፡፡ የአገልግሎት ዘርፍ ዋና ዋና አመልካቾች በተለይም የቱሪስት ፍሰት እና የአየር ትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች (የተሳፋሪ እና የጭነት ማጓጓዣ) እና የብድር አቅርቦት መሻሻሎች ምክንያት ዘርፍ በመደገፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡ እንዲሁም የወርቅ ወጪ ንግድ፣ የካፒታል እና የጥሬ ዕቃ ምርቶች ገቢ ንግድ ዕድገቱን እንደሚያጠናክሩ ይገመታል፡፡
የገንዘብ ሁኔታ፡- መሠረታዊ ገንዘብ (base Money) በመስከረም ወር 2019 መጨረሻ 87.2 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት ያስመዘገበ ሲሆን ይህም ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ከተመዘገበው 72.6 በመቶ ዕድገት ጋር ሲነፃፀር መጠነኛ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ለመሰረታዊ ገንዘብ ዕድገት የብሔራዊ ባንክ ከወርቅ ግዢ ጋር በተያያዘ የውጪ ምንዛሪ ክምችት መጨመሩ እና ከዚሁ ጋር ተያይዞ ወደ ባንኮች የገባው የጥሬ ገንዘብ መጨመር እንደዋነኛ ምክንያት እንደሚጠቀስ ኮሚቴው ተገንዝቧል፡፡ በተመሳሳይም፣ የጠቅላላ ገንዘብ አቅርቦት (Broad Money) ዓመታዊ ዕድገት ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 33.2 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 40.2 በመቶ ሆኗል፡፡ ይህም ከሚጠበቀው የሃገር ውስጥ ምርት (GDP) እድገት ጋር ሲነጻጸር ከፍ ያለ ነው፡፡ ከሪፎርሙ በፊት ለጠቅላላ የገንዘብ ዕድገት የአገር ውስጥ ብድር ከፍተኛ ድርሻ የነበረው ሲሆን በአሁኑ ወቅት በዋናነት የተጣራ የውጭ ምንዛሪ ክምችት (Net Foreign Asset) ክፍ ያለ ድርሻን ይዟል፡፡
የወለድ ተመን ሁኔታ፡- ኮሚቴው ባደረገው ግምገማ የመንግስት ግምጃ ቤት ሰነዶች አማካይ የወለድ ምጣኔ እንዲሁም ባንኮች እርስ በእርስ የሚበዳደሩበት የ7-ቀን የባንክ ለባንክ የገንዘብ ገበያ አማካይ የወለድ ተመኖች ከግንቦት ወር 2018 ጀምሮ ማሽቆልቆል ማሳየታቸውን ተገንዝቧል፡፡ ይሁን እንጂ የባንኮች የቁጠባ እና የማበደሪያ የወለድ ተመን ግን ከባለፈው ሩብ ዓመት መጨረሻ ለውጥ እንደሌለው ታይቷል፡፡ ሌሎች ምክንያቶች እንዳሉ ሆኖ ለአጭር ጊዜ የወለድ ተመኖች መቀነስ ባንኮች በብሔራዊ ባንክ ያላቸዉ ትርፍ ገንዘብ (excess liquidity) በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ነዉ፡፡
የባንክና የፋይናንስ ዘርፍ፡- በ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የባንክ ዘርፉ ዝቅተኛ የተበላሸ ብድር እና በቂ ካፒታል ያለው በመሆኑ ጤናማና የተረጋጋ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ ባንኮች በሩብ በጀት ዓመቱ የተጣራ የተቀማጭ ገንዘብ ክምችት 85.4 በመቶ እና አጠቃለይ የብድር ክምችት ደግሞ 42.6 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡ ምንም እንኳን የብድር ዕድገት ላይ ተጥሎ የነበረው ገደብ (credit cap policy) ቢነሳም እና ባንኮች ከፍተኛ ቁጠባ ቢሰበስቡም፣ የሰጡት አዲስ ብድር (Disbursment) ከአጠቃላይ ተቀማጭ እና ተመላሽ አኳያ ሲነጻጸር ከባለፈው ሩብ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ተቀራራቢ ነዉ፡፡
የበጀት ሁኔታ፡- የበጀት ፖሊሲ ስርዓት ጥንቃቄ የተሞላበት እና ከብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ጋር የተጣጣመ እንዲሁም ከአጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ጋር የተናበበ እንደነበር ኮሚቴው ተገንዝቧል፡፡ መንግሥት በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዉ ሩብ ዓመትም ምንም ብድር ከብሔራዊ ባንክ ስላልወሰደ ያለ ብሔራዊ ባንክ ብድር ቆይታዉ ከ27 ወራት በላይ ሆኗል፡፡ ይህምሁኔታ የዋጋ ግሽበቱን ለማረጋጋት አስተዋጽኦ ማድረጉን ኮሚቴው አስተውሏል::
የውጭ ኢኮኖሚ ዘርፍ፡- የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከአምና ተመሳሳይ ሩብ ዓመት ጋር ሲነጻጸር የውጭ ሚዛን አጠቃላይ ትርፍ (Overall Surplus) በመጠኑ ቅናሽ ያሳየ ቢሆንም፣ ከሪፎርሙ በፊት ከነበረው አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሻሻል ማሳየቱን ኮሚቴው ተገንዝቧል፡፡ በሩብ ዓመቱ የሸቀጦች ወጪ ንግድ በተለይ የወርቅ እና የቡና አፈጻጸም አወንታዊ ዕድገት ያሳዩ ሲሆን የገቢ ሸቀጦችም እድገት ከፍተኛ ነበር፡፡ ምንም እንኳን የንግድ ሚዛን ጉድለት ቢሰፋም በግለስቦች ሃዋላ (Private Transfers) እና በካፒታል ሂሳብ (Capital Account) የተመዘገበው ዕድገት አጥጋቢ በመሆኑ ለአጠቃላይ የክፍያ ሚዛን (Overall Balance of Payments) ትርፍ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
የዓለም አቀፍ ሁኔታዎች፡- የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) የጥቅምት 2026 ትንበያ የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት በ2026 3.1 በመቶ እና በ2027 ደግሞ 3.4 በመቶ እንደሚሆን ተገምቷል፡፡ የዓለም አቀፍ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ደግሞ በ2026 ወደ 4.7 በመቶ እንደሚደርስ እና በ2027 ወደ 4.1 በመቶ እንደሚቀንስ ተገምቷል፡፡ በዓለም ዓቀፉ እየታየ ያለው የግጭቶች ቀጣይነት፣ የኢነርጂ ዋጋ ጭማሪ፣ እንደገና እየተቀሰቀሱ ያሉ የንግድ ውጥረቶች እና የፋይናንስ ተጋላጭነቶች በኢኮኖሚ እይታው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ያሳያል፡፡ ይህ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የነዳጅ አስመጪ ኢኮኖሚዎች የአቅርቦት መቋረጦች፤ የምርት እና የመጓጓዣ ወጪዎችን እንዲንሩ ያደርጋሉ፡፡ የተጽእኖው መጠን የሚወሰነው መስተጓጎሉ በሚቆይበት ጊዜ ፣ የኢነርጂ አቅርቦቱ በሚስተካከልበት ፍጥነት እና የዋጋ ጭማሪው በስፋት ወደ አገር ውስጥ የዋጋ ጭማሪ የሚተላለፍበት ደረጃ እና የዋጋ ንረት ግምት ላይ ነው፡፡
የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ትንተናና ምክረ-ሀሳቦች
ኮሚቴው በግምገማው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በመካከለኛ ጊዜ ለማሳካት የያዘውን የነጠላ አሃዝ የዋጋ ግሽበት ዓላማ ለማሳካት ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አጽንኦት ሰጥቶበታል፡፡
በዚህ መሠረት ኮሚቴው ሶስት የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ለቦርድ አቅርቦ አስወስኗል፡፡
አንደኛ፡ እየታየ ባለዉ መጠነኛ ልቅ የገንዘብና ፋይናንስ ሁኔታ ብሎም በባለሁለት አሃዝ ይቆያል ተብሎ የተተነበየዉን የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲን ማስቀጠል አስፈላጊ በመሆኑ፣ የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ወለድ ምጣኔ ባለበት 16 በመቶ ሆኖ እንዲቀጥል እና የ±3 በመቶኛ ነጥብ ልዩነት ክልል (Band) ሳይለወጥ እንዲቆይ ተወስኗል፡፡
ሁለተኛ፡ ባንኩ እየተገበረዉ የሚገኘው መደበኛ የባንኮች የመጠባበቂያ ተቀማጭ እንዳለ ሆኖ፤ የብድር ዕድገት መስፋፋት በዋጋ ግሽበት ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድር ሆኖ ሲገኝ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚያካሂደው መደበኛ ግምገማ መሠረት የእያንዳንዱን ባንክ የብድርና የተቀማጭ ሂሳብ ጥመርታ (loan-to-deposit ratio) ላይ በመመርኮዝ የተለየ የመጠባበቂያ ተቀማጭ (targeted reserve requirement) መተግበሩን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
ሦስተኛ፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ አቋሙን ለማስቀጠል በፖሊሲ ማዕቀፉ ውስጥ ያሉትን ሁሉንም ቀጥተኛ ያልሆኑ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎችን መጠቀሙን የሚቀጥል ይሆናል፡፡፡፡ በተለይም በኢኮኖሚው ውስጥ ከሚጠቀበቀው በላይ ትርፍ ገንዘብ (Excess Liquidity) ሲኖር ባንኩ ከባንኮች ጋር የሚያደርገውን የጨረታ ሰነድ-ግብይት (Open Market Operations) መጠቀሙን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ኮሚቴው በጥር ወር 2019 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ፣ አስፈላጊ ሁኔታ ከተፈጠረም ከዚያ ቀደም ብሎ ይሰበሰባል።
የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
ጥቅምት 24 ቀን 2019 ዓ.ም.












