NBC Ethiopia
በ – ሃና ደሴ
እየጨመረ የመጣውን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል ፍላጎት ለሟሟላት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበርካታ ቦታዎች የኤሌክትሪክ ቻርጅ መሙያ ጣቢያዎችን በመገንባት ለአገልግሎት እያቀረበ ይገኛል ። በዛሬው ዕለትም አዲስ አበባን ጨምሮ በቢሾፍቱ ፣ በአዳማ ፣ በሀዋሳ ፣ በባቱ እና በሞጆ ያስገነባቸውን 11 የኤሌክትሪክ ቻርጅ መሙያ ጣቢያዎች አመርቆ አገልግሎት አስጀምሯል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ ጌቱ ገረመው ፕሮጀክቶቹ አረንጋዴ ኢትዮጵያን ለመፍጠር በሚደረገው ጉዞ ውስጥ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እያደረገ ያለውን ብርቱ ጥረት የሚያሳይ መሆኑን ገልፀዋል።
ዋና ስራ አስፈፃሚው በአዲስ አበባ የተመረቁት 5 የኤሌክትሪክ መሙያ ጣቢያዎች እያንዳንዳቸው በአንድ ጊዜ 12 ተሽከርካሪዎችን የማስተናገድ አቅም እንዳላቸው የገለፁ ሲሆን በሌሎች ዋና ዋና ከተማዋች ላይ የተገነቡት ጣቢያዎች ደግሞ እያንዳንዳቸው 6 ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ የሚያስተናግዱ ስለመሆናቸው ተናግረዋል።

ለአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችም ለአንድ ኪሎ ዋት የክፍያ ዋጋ 14 ብር መሆኑንም ጠቁመዋል። በቀጣይም በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዙር በሀገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች ላይ መሰል የኤሌክትሪክ ቻርጅ መሙያ ጣቢያዎችን ለመገንባት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።

የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አለማየው አሰፋ በከተማዋ የተገነቡት 2 የኃይል መሙያ ጣቢያዎች ለከተማዋ ነዋሪዎችም ሆነ ለቱሪስቶች መልካም ዜና የሆነ እና ከተማዋ የምትፈልገውን አላማ ለማሳካት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚኖረው ነው ብለዋል። በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ ለመሰል የልማት ተግባራት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደግ ገልፀዋል።













