ኤርትራ የተዘጋች ትልቅ እስር ቤት ናት – የብርጌድ ንሃመዱ አመራሮች
በኤንቢሲ ኢትዮጵያ «ጊዜ ግስ» ፕሮግራም ላይ ቆይታቸውን ያደረጉት የብርጌድ ንሃመዱ አመራሮች አቶ በየነ ገ/እግዚአብሔር እና አቶ ዳዊት ይብራህ የኤርትራን አሁናዊ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ ሲያስረዱ “ኤርትራ ለዜጎቿ ነፃነታቸውን ነፍጋ የምታኖር በር እና መስኮት የሌላት ትልቅ እስር ቤት ናት” ይላሉ::

የኤርትራ ህዝብ ከ1993 (እ.ኤ.አ.) ጀምሮ ያለ ህገ-መንግስት ሲመራ፣ ምርጫ በሌለበት ሲኖር የፍርሃት ቀንበር ተጭኖበት ለመብቱ ሳይቆም ቢኖርም ከዚህ አይነት ኋላ ቀር አመራር እና የፖለቲካ አካሄድ ህዝቡ ነፃ መውጣት አለበት ያሉት አመራሮቹ ለትውልድ ሃገራቸው ነጻነት ለማምጣት የፖለቲካ እንቅስቃሴን አጠናክረው መቀጠላቸውን አስታውስቀዋል፡፡
ብርጌድ ንሃመዱ በ2022 (እ.ኤ.አ.) በውጪ ሃገራት ከሚኖሩ ዲያስፖራ ኤርትራዊያን በግዴታ የሚሰበሰብ የ2% የገቢ ማሰባሰብን እና በሃገርም ውስጥም ሆነ በውጪ የሚኖሩ ኤርትራዊያን የሚደርስባቸውን ጭቆና በመቃወም በውጪ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ሲሆን፣ በተለያዩ አህጉራት መሰረት መጣሉን የብርጌዱ አመራር ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት ወደ አፍሪካ የመጣው አንቅስቃሴው፣ ኤርትራ ከሌላው ዓለም ጋር ባላት ግንኙነት የተዘጋ አቋም ቢኖራትም፣ ብርጌድ ንሃመዱ “ሥር ነቀል ለውጥ በኤርትራ” በሚል መሪ ቃል በኤርትራ እንቅስቃሴ ጀምሯል ነው ያሉት፡፡
ህዝቡ ለዓመታት የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ለውጥ አይቶ አያውቅም:: ስለሆነም ኤርትራዊያን ልባቸው ከሃገራቸው መራቁን እና በፍርሃት ታስረው መኖራቸውን ሲያብራሩ፣ በሃገራቸው ያለውን ጥብቅ አምባገነናዊ አመራር ለመቃወምም ሆነ ለመቀየር መብት ማጣታቸውን ያስረዳሉ፡፡ ይሄንም ገፊ ምክንያት ተቃውሟቸውን ለመግለጽ በድብቅ የተለያዩ መልእክቶችን በከተማዋ መንገዶች ላይ በመስቀል እየገለጹ እንደሆነ ይናገራሉ::
የሰው ልጆች መብት ተገፎ፣ ወጣቶችን ከትምህር ይልቅ ወደ ጦር ውጊያ ስልጠና በማስገባት፣ ቀን ከለሊት የሚሰሩ ዜጎች ሃብት ማከማቸት በማይችሉበት፣ ከብዙ አስርት ዓመታት በኋላም ቢሆን ቆማ የቀረችው ኤርትራ፣ ዜጎቿ የመኖር ፍላጎት አጥተው “የጥንት ጠላታችሁ ናት” እየተባሉ ያደጉባት ኢትዮጵያ መሸሸጊያቸው ሆናለች፡፡
የብርጌድ ንሃመዱ አመራሮች አክለውም፣ የኤርትራ ሰራዊት እና ህዝብ በኢትዮጵያ ድንበር በኩል ጥቂት ክፍተት ቢያገኝ ሸሽቶ ወደ ኢትዮጵያ ለመቀላቀል ፍላጎታቸው ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
የአብስራ ተፈራ












