
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ላፍቶ መድኃኒያለም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ዋና መምሪያ አዛዥ ኮማንደር አራጌ እሸቴ፣ የክፍለ ከተማው ሠላም እና ጸጥታ አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ ደረጀ ድሪብሳ፣ የክፍለ ከተማው ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት ኃላፊ መቶ አለቃ ቦጋለ አለሙ፣ በዋና መምሪያው ስር ያሉ የመምሪያ ኃላፊዎች፣ የኃይማኖት አባቶች እና የአካባቢው ነዋሪዎች በተገኙበት ከአራት ሺህ በላይ የሺሻ እቃዎች እና 40 ኪሎ ግራም ካናቢስ የተባለ አደንዛዥ እጽ ተወግዷል።
የዋና መምሪያው አዛዥ ኮማንደር አራጌ እሸቴ እንደገለጹት በዋና መምሪያው እና በስሩ ካሉ መምሪያዎች ከ2013 ዓ/ም ጀምሮ በኤግዚቢትነት ተይዘው የነበሩ ጥራታቸውን ያልጠበቁና በህገ ወጥ መንገድ የተዘጋጁ የዋጋ ግምታቸው 112, 503,960 ብር የሚሆን 500 ካርቶን የልብስ ሳሙናዎች፣ 4110 የሺሻ እቃዎች እና 40 ኪሎ ግራም ካናቢስ የተባለ አደዛዥ እጽ መወገዱን ገልጸዋል፡፡
በክ/ከተማው ለሠላምና ፀጥታ ስራው እንዲሁም ደህንነት ስጋት የሆኑ ጉዳዮች በጥናት ተለይተው ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የገለፁት ዋና መምሪያ አዛዡ የፖሊስ ስራ ያለ ህብረተሰቡ ተሳትፎ ውጤታማ ስለማይሆን ህብረተሰቡ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
የክፍለ ከተማው ሠላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደረጀ ድሪብሳ በበኩላቸው ፖሊስ በኤግዚብትነት ይዞ ያስወገዳቸው ህብረተሰቡን የሚጎዱ፣ ለሠላም እና ጸጥታው ስጋት የሆኑ ነገሮች መሆናቸውን ገልጸው፤ ፖሊስ አስቀድሞ ወንጀልን ከመከላከል ጀምሮ በቁጥጥር ስር እስከ ማዋል የህግ የበላይነትን እያረጋገጠ መገኘቱ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል፡፡
በቦታው የተገኙ የኃይማኖት አባቶች እና የአካባቢዉ ነዋሪዎች የተወገዱት ኤግዚቢቶች በማህበረሰቡ ላይ የጤና ችግር የሚያስከትሉ እና ወንጀልን ለመፈጸም አነሳሽ የሆኑ ነገሮች በመሆናቸው ፖሊስ በሰራው ስራ መደሰታቸውን ገልጸው ከፖሊስ ጎን በመሆን የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም ተናግረዋል።












