
2ኛው ሀገር አቀፍ የህብረት ሥራ ማህበራት ንቅናቄ በሀገሪቱ 6 ከተሞች መካሄድ ጀምሯል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ፥በኢትዮጵያ የኅብረት ሥራ ማህበራት የሪፎርም ንቅናቄን በቀበሌ/ማህበረሰብ ደረጃ ለማድረስ እና በገጠር ልማት እና ግብርና ትራንስፎርሜሽን ያላቸውን ሚና ለማጠናከር ያለመ ምክክር ከባለ ድርሻ አካላት ጋር እያካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ፥ በኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ገልጸው፥ በዚህ ሂደት የህብረት ሥራ ማህበራት የሚጫወቱት ሚና የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
ነገር ግን ማህበራቱ አሁንም በሚፈለገው ልክ መስራት ላይ ሰፊ ክፍተቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።
በሀገሪቱ ከነበሩ 125 ሺ በላይ የህብረት ሥራ ማህበራት ከ31ሺ የሚሆኑት በተገቢው ሁኔታ ባለመስራታቸው፥ ከሶስት አመት ወዲህ በተደረገ ሪፎርም በስም ብቻ የታወቁ ነገር ግን የታወቀ አድራሻ የሌላቸው እንዲሁም ሪፖርት የማይልኩ የህብረት ሥራ ማህበራት መገኘታቸውን ገልጸዋል።
5ሺ የሚሆኑት ራሳቸውን ችለው መቆም የማይችሉ በመሆናቸው እንዲዋህዱ ተደርጓልም ነው ያሉት።
አሁን ላይ ካሉ አጠቃላይ 89ሺ ማህበራት ውስጥ 66 በመቶ የሚሆኑት በርካታ ክፍተት የተያባቸው ሆኖ በመገኘቱ ችግሮቹን ለመፍታት የጋራ አቋም ተይዟል ብለዋል።
የህብረት ሥራ ማህበራት ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር ጌትነት ታደሰ በበኩላቸው፥ የህብረት ስራ ማህበራት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚጫወተው አስተጽኦ የጎላ መሆኑን ገልጸው፥ እንደ ሀገር የተጀመረው የህብረት ስራ ሪፎርም የዘርፋን አቅም ለማሳደግ የጎላ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።
የህብረት ሥራ ማህበራቱን አቅም በማጎልበት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፥ አምራቹን ከሸማች ማገናኘት ላይ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፥ ለስምንት ቀናት በሚቆየው እና ከ4ሺ በላይ ተሳታፊዎች ንቅናቄም የዘርፋን ችግሮች ለመቅረፍና ለመፈተሽ የቤት ስራ የሚወሰድ መሆኑን አመላክተዋል።
በንቅናቄ ዘመቻው የኅብረት ሥራ ማህበራት ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታ፣የህብረት ሥራ ማህበራትን ማዘመን፣ የህብረት ሥራ ግብይትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ይመከራል ተብሏል።
በ-ሰላማዊት ወንድወሰን












