February 11, 2026
አፍሪካ ምጽዋት ሳይሆን ትክክለኛ የልማት አጋር የሚያስፈልጋት የበርካታ ጸጋና የተስፋ ምድር መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።

48ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ’’ዘላቂ የውሃ ኑረትና ንጽህና ስርዓት፤ ለአጀንዳ 2063 ስኬት” በሚል መሪ ሃሳብ በሕብረቱ ዋና መስሪያ ቤት አዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፤ አፍሪካ በመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት፣ በአየር ንብረትና በዓለም አቀፍ የፋይናንስ መዋቅር ማሻሻያ ላይ የጋራ አቋም ይዛለች ብለዋል። ይህም የአፍሪካን ዓለም አቀፍ ሚና ለማሳደግም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ በተካሄደው የቡድን-20 ጉባኤ ላይ ጎልቶ መታየቱን ገልጸዋል።
ሀገር አቀፍ ምርጫ ከተካሄደባቸው በርካታ አፍሪካ ሀገራት መካከል የጊኒ ሪፐብሊክና የጋቦን ሪፐብሊክ ሕገ-መንግስታዊ ስርዓትን በመመለስ ወደ ሕብረቱ መቀላቀላቸውን በበጎ አንስተዋል። አሁንም የአፍሪካ ሕብረትን መሠረት የሚያናጉ ኢ-ሕገ-መንግስታዊ የመንግስት ለውጦችና የዓለም አቀፍ ጂኦ-ፖለቲካዊ ሁኔታ የአህጉሪቷን ሰላምና ደኅንነት እየተፈታተነ መሆኑን አስገንዝበዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃም የቴክኖሎጂ የበላይነት፣ የማዕድን ሃብትና የሎጂስቲክስ መስመሮች ቁጥጥርና ከፍተኛ ውድድር እያየለ መምጣቱን አስረድተዋልአፍሪካን በፉክክርና የፍላጎት ማስፈጸሚያ ሜዳነት በሚመለከቱ ትላልቅና መካከለኛ ኃይሎች መነሻነት ከየትኛውም አቅጣጫ የሚመጡ ችግሮችን ለመከላከል ሕብረትን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

አፍሪካ ምጽዋት ሳይሆን እውነተኛ የልማት አጋር ያስፈልጋታል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ለዚህም ለአህጉራዊ አንድነትና የጋራ የልማት ዓላማዎች ስኬት በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል። በአጀንዳ 2063 የምንፈልጋትን አፍሪካ እውን ለማድረግ ተግባራዊ የተደረገው የአፍሪካ አሕጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት በብዙ መልኩ በተሻለ ሁኔታ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ሲሉ አብራርተዋል። በአህጉሪቷም በአየር ንብረት ለውጥ ቅነሳ፣ በጤና፣ በግብርና መሰል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮችም የተረጋጋ ዕድገት እየተመዘገበ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም የአፍሪካ ሕብረትን ገንቢ ሚና የበለጠ በማጠናከር ለጋራ የተሻለ ዕጣ ፋንታ በአንድነትና በቁርጠኝነት መስራት እንደሚጠይቅ አስረድተዋል። የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካዊ መፍትሔ እልባት በመስጠት ለዘላቂ ሰላምና ሕገ-መንግስታዊነት መርሆች በመገዛት የበለጸገች አህጉር መገንባት እንደሚገባም አብራርተዋል። በተጨማሪም አፍሪካ በዓለም አቀፍ ተቋማት ውሳኔዎች ላይ ትክክለኛው ቦታ እስኪቸራት ድረስ የሚደረጉ የዓለም አቀፍ የትብብር ጥያቄዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የአፍሪካ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት የካቲት 7 እና 8 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚካሄደው 39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል። በስብሰባው ላይ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ፣ የአንጎላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ስብሰባ ሊቀመንበር አምባሳደር ቴቴ አንቶኒዮ እና የአባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተገኝተዋል።
:: :: ::












