January 26, 2026
በኢትዮጵያ ጥቅምት ወር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጂንካ ከተማ የማርበርግ በሽታ መከሰቱ ይታወሳል። በበሽታው የላቦራቶሪ ምርመራ ከተደረገላቸው ከ3 ሺህ በላይ ዜጎች ውስጥ አስራ አራት ሰዎች በበሽታው የተያዙ ሲሆን አምስቱ ሲያገግሙ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ደግሞ ማለፉ ተገልጿል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የማርበርግ ቫይረስን ለመቆጣጠር በተከናወኑ ተግባራት የአለም ጤና ድርጅት የሚያስቀምጠውን የ42 ቀናት ከበሽታ ነፃ የመሆን ጊዜ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ተከትሎ በሽታውን ሙሉ ለሙሉ ማስወገድ መቻሉን ይፋ አድርጓል። በሽታውን ሙሉ ለሙሉ ማስወገድ መቻሉን ተከትሎ በተዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ይህ የተመዘገበው ድል ከጤናው ዘርፍ የተሻገረ መሆኑን አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስ በሽታን ሙሉ ለሙሉ ማስወገድ መቻሏ ድንገተኛ አደጋዎችን የመከላከል አቅሟ በከፍተኛ ደረጃ ማደጉን የሚያሳይ ነው ብለዋል። የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው ወረርሺኙ ያደርስ ከነበረውን ውድመት መከላከል መቻሉን ገልፀዋል።

የመጨረሻው ታካሚ በላብራቶሪ ምርመራ ነፃ መሆኑ ከተረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ ለ42 ተከታታይ ቀናት ምንም አይነት የበሽታው ተጠቂ አለመመዝገቡን ገልፀው በየስፍራው በሽታውን ለይቶ የመቆጣጠር ስራ በመሰራቱ የተገኘ ውጤት መሆኑን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የአለም ጤና ድርጅት ተወካይ ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ይህ ውጤት ኢትዮጵያ ያላትን ሀገር አቀፍ በሽታ የመከላከል ዝግጁነትን የሚያመላክት መሆኑን ገልፀዋል።
በ – አክረም ኑርያ












