
ላለፉት 100 ዓመታት በህብረተሰብ ጤና ላይ የሚከሰቱ የጤና ችግሮችን ሲሰራ የቆየዉ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በርካታ ሃገር በቀል ስራዎችን እና ማህበረሰብ ተኮር የሆኑ ዘርፈ ብዙ የጤና አካታች ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን አስታዉቋል።
ኢንስቲትዩቱ መቶኛ ዓመቱን አስመልክቶ ለሚዲያ ባለሙያዎች እና ለዘርፉ አካላት ተቋሙ ስለሚሰጣቸዉ ግልጋሎቶች ማብራሪያ የሰጠ ሲሆን የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ምህዳር ምን ላይ እንዳለም አስጎብኝቷል።
ይህን ያመላከተ የዉይይት እና የጉብኝት መድረክ ያዘጋጀው ኢንስቲትዩቱ በቀጣይ ሊሰራ ስላሰባቸዉ ስራዎች እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ያተረፉትን የላብራቶሪ ማዕከሎቹ ሃገርን ከማሳደግ አኳያ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳላቸዉ ተገልጿል።

ኢንስቲትዩቱ በተጨማሪነት ያስገባቸዉ የላብራቶሪ ማሽኖች የተወሰኑት በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ብቸኛ የሆኑ ሲሆን ከ700 ሚሊየን ዶላር በላይ የሆኑ እና ዓለም የደረሰችበትን ቴክኖሎጂ የሚከተሉ መሆናቸዉን ተመላክቷል።
በተጨማሪም በመድረኩ የኢንስቲትዩቱ የ100 ዓመታት ጉዞ በወፍ በረር የተቃኘ ሲሆን ምርምር ስራዎች፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ወይም ወረርሽኞች መከላከልና መቆጣጠር ተግባራት ብሎም በኢንስቲትዩቱ የሚካሄዱ በርካታ ክንውኖችን የተቃኙ ሲሆን የተቋሙ አመራሮች ፣ ባለድርሻ አካላት እና አጋር ድርጅቶች በመድረኩ ታድመዉበታል።












