
አዲሱ የኢትዮጵያ ፖስታ የሳጥን አልባ የመልዕክት አገልግሎት (Virtual P.O. Box) በባሕር ማዶ ወይም በኢትዮጵያ ውስጥ መልዕክትን በኦን ላይን እንዲቀበሉ የሚያስችል መሆኑ እና መተግበርያውንም በቴሌብር ሱፐር አፕ ማግኘት እንደሚቻል ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ፖስታ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳግማዊ አልዬ የዲጂታል ፖስታ አገልግሎቶች ይፋ መደረጋቸው በአካል መገኘት ሳይጠበቅ ባሉበት ሆነው መገልገል የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የኢንደስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በበኩላቸው በኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በመልዕክተኞች የተጀመረውን ታሪካዊ ሒደት አስታውሰው ኢትዮጵያ በ131 ዓመታት ሒደት የፖስታ አገልግሎት ዘመናዊ ሒደቱ እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም በአሁኑ ወቅት መንግስት ዲጂታል 2025ን በማሳካት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን እውን ለማድረግ የዲጂታል ዘርፍ የኢኮኖሚው የማዕዘን ድንጋይ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል።
የመንግስት የልማት ድርጅት የሆነው የኢትዮጵያ ፖስታ መደበኛ ጥቅል እና ፈጣን አገልግሎቶችን በመስጠት በሀገር ውስጥ ከ1ሺህ በላይ ቅርንጫፎች በዓለም ዓቀፍ ደረጃ 194 መዳረሻዎችን በመፍጠር አገልግሎቱን ወደዲጂታል ዘርፍ እያሳደገ ይገኛል።
በ-ፍቅረሚካኤል ዘየደ












