
የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ በክልሉ የሚገኙ ቋንቋዎችን ለማልማት፣ ጥበቃ ለማድረግ እና የአጠቃቀም ሥርዓታቸውን ለማሳደግ እየተሠራ ነው አለ።
በክልሉ የሚገኙ ቋንቋዎች ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ሥርዓትን በተመለከተ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን በባህርዳር ከተማ እየመከሩ ነው።
የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ መልካሙ ጸጋዬ በመድረኩ እንዳሉት፤ ቋንቋዎች ጥበቃና እንክብካቤ የሚፈልጉ ሀብቶች ናቸው።
የቋንቋዎች የአጠቃቀም ሥርዓት ካልተበጀ ከጊዜ ወደ ጊዜ በውጫዊና ውስጣዊ ተጽዕኖዎች ምክንያት ከማኅበረሰብ ማንነቱ መገለጫነት እየወጡ ሊዳከሙ ይችላሉ፤ ስለሆነም ለቋንቋዎች በጥናት ላይ የተመሰረተ እንክብካቤና ጥበቃ ለማድረግ የቋንቋ ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም አዋጅ በማውጣት ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ መምህርና ተመራማሪ ማረው ዓለሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ባለሙያዎችን ባሳተፈ መንገድ ለቋንቋዎች እንክብካቤ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
የቋንቋዎች አጠቃቀም ችግር በእውቀት ማነስ፣ በውጭ ቋንቋ መሰየምና መጠራት የመፈለግ የተዛባ አመለካከት፣ በግዴለሽነት፣ የተዛባ የቋንቋ አጠቃቀም በሚፈጥሩ ላይ ተጠያቂነት አለመኖር እና በመሳሰሉት የተነሳ እንደሚከሰት አስረድተዋል።
ክልሉ ቋንቋዎችን ለመንከባከብ፣ ለማሳደግ እና የአጠቃቀም ሥርዓት ለማዘጋጀት ከምሁራን፣ ከተቋማት እና ከሌሎች ክልሎች ልምድ በመቀመር የቋንቋዎች ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም አዋጅ ለማዘጋጀት እየሠራ መሆኑ ተገልጿል።












