December 23, 2025
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሰራተኞች የቤት መገንበያ ብድር ለማቅረብ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ስምምነት አካሂዷል። ባንኩ 27 ቢሊየን ብርን ለብድር ያቀረበ ሲሆን ለአየር መንገዱ ሰራተኞች የቤት ግንባታ የሚውል መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮርፖሬት አገልግሎቶች ኤክስኪዩቲቭ ምክትል ፕሬዚዳንት ኤፍሬም መኩሪያ ባንኩ ላለፉት ዓመታት ባንኩ ለታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች እና ለግሉ ዘርፍ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለብድር መስጠቱ ገልፀዋል።458 ቢሊየን ብር ብድር ባንኩ መስጠቱን ያነሱት ምክትል ፕሬዝዳንቱ 88 በመቶ የሚሆነው ለግሉ ዘርፍ፤ 12 በመቶ ደግሞ ለመንግስት መሰጠቱን አብራርተዋል።

ላለፉት 80 አመታት ኢትዮጵያን ከመላው አለም ጋር ሲያገናኝ የቆየው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው አየር መንገዱ ከዚህ ቀደም 1200 ሰራተኞቹን የቤት ባለቤት ማድረጉን አንስተዋል። በአሁኑ ወቅትም 5ሺ ለሚሆኑ ሰራተኞቹ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚውለውን የ27 ቢሊየን ብር የብድር ስምምነትን ነው በዛሬው እለት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የፈፀመው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ስምምነቱ ታሪካዊ መሆኑን በመግለፅ ላለፉት ዓመታት በሁሉቱ ተቋማት መካከል የነበረውን ጠንካራ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያደርስ ነው ብለዋል።
በ – ሀሴት ኃይሉ












