
የኢትዮጵያን የኒውክሌር ኃይል ልማት መርኃ ግብር ማስጀመሪያና የኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን ሥራ ማስጀመሪያ የምክክር መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሌር ልማት መርኃ ግብር ከዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ማዕቀፎች ጋር በማጣጣም የሚተገበር መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያም በሰው ሰራሽ አስተውሎትና ቴክኖሎጂ ልማት በአዲስና አስፈላጊ የኢንዱስትሪ አብዮት ጉዞ ላይ እንደምትገኝ የተናገሩት ሚኒስትሩ የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ልማት በአስተማማኝ፣ የረጅም ጊዜና ንጹህ የኃይል ምንጭነት ከፍተኛ ትኩረት እያገኘ መምጣቱን አንስተዋል።
የኒውክሌር ኃይል ለዘላቂ ብልጽግና መሠረት ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና ብዙ የሕዝብ ቁጥር የኃይል ፍላጎት ለማሟላት የረጅም ጊዜና ስትራቴጂካዊ የመሠረተ ልማት ግንባታ ኢንቨስትመንቶችን ማስፋት አስፈላጊ ሆኗል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ ዳታ ማዕከላት፣ ባቡሮችና ተሸከርካሪዎች እንደ ኒውክሌር ኃይል ባሉ ከታዳሽና አስተማማኝ የኃይል ምንጮች በሚገኝ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩባት ሀገር የማድረግ ጉዞም በወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ከዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋርም የኢትዮጵያን ብሔራዊ የኒውክሌር ልማት መርሃ ግብር የደህንነትና ግልጽነት ደረጃ ለማስጠበቅ እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የአፍሪካ ኩራት የኢትዮጵያ የአቬሽን ኢንዱስትሪ እና የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬትም በሰላማዊ የኒውክሌር ኃይል አማራጭ ያላትን የብልጽግና ተምሳሌት ሕልም ለማሳካት ይሰራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።












