December 2, 2025
በባለሃብቶች ይነሱ ለነበሩ ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሽ በመሰጠቱ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ መጨመሩን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ። በሂደት ከተመለሱ ጥያቄዎች መካከል 14 ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች መቀየር መቻሉ አንዱ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ ይነሱ ለነበሩ ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሽ መሆኑን አስረድተዋል። እንዲሁም ከውጭ ምንዛሪ ጋር ተያይዘው ይነሱ ለነበሩ ጥያቄዎች በኢኮኖሚ ማሻሻያው መሠረት ለውጦች መገኘታቸውን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ መዳረሻዎቹን ማስፋቱ ድርጅቶች በቀላሉ ምርታቸውን ወደ ተለያዩ ሀገራት ለመላክ እንዳስቻላቸውም ጠቅሰው፣ በነዚህ የማሻሻያ ሥራዎች እገዛ በእ.ኤ.አ 2024/2025 ከ4 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ማስመዝገብ መቻሉን አረጋግጠዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት ዕድሎች ለማስተዋወቅ የሚያስችል የአምስት ዓመት የኢንቨስትመንት ስትራቴጂ በማውጣት ወደ ሥራ መገባቱን ኢዜአ ዘግቧል።












