ኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና የኢኮኖሚ ትብብራቸውን ለማጎልበት እንደሚሰሩ አስታወቁ።
የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት ኢንቨስትመንት ፎረም ዛሬ በፈረንሳይ ፓሪስ መካሄድ ጀምሯል። ፎረሙ በኢትዮጵያ እና አውሮፓ ህብረት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር ማጠናከርና አዳዲስ የኢንቨስትመንት እድሎችን መጠቀም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ በፎረሙ ላይ የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም በዝርዝር አስረድተዋል። ሪፎርሙ የግል ኢንቨስመንት መሳብ እና ኢትዮጵያ ከዓለም ኢኮኖሚ ጋር ያላትን ትስስር የበለጠ ማጠናከርን ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
በፎረሙ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉ ባለስልጣናት የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ህብረት የኢኮኖሚ ትብብር እያደገ መምጣቱን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ምቹነትን ለማሻሻልና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብን አላማ በማድረግ እያደረገቻቸው ያሉ የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ ምክክሮች መልካም የሚባሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በፎረሙ የአውሮፓ ህብረት የ”ግሎባል ጌትዌይ ፓርትነርሺፕ” ማዕቀፍ ያለው ጠቀሜታም ተነስቷል። ማዕቀፉ የሁለቱ ወገኖች ትብብር ለማጠናከርና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽንና ዘላቂ እድገት የሚውል የአውሮፓን ኢንቨስትመንት ለማሰባሰብ እንደሚያግዝ ተመላክቷል።
በመክፈቻው ስነ ስርዓት ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)፣ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ፣ የአውሮፓ ኮሚሽን የአፍሪካ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ጌዛ ስትራመር፣ የፈረንሳይ የወጪ ንግድ እና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር መልዕክተኛ ኒኮላስ ፎርሲየር፣ የሜዴፍ ኢንተርናሽናል ምክትል ፕሬዝዳንት ፋብሪስ ላሳች፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ባለሀብቶች እና የንግድ መሪዎች ተገኝተዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።












