የ2018 ዓ.ም የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ 911 ሺህ 200 የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ በማድረግ 9 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የሚገመት የመንግስት ወጪ ለማዳን እቅድ የታየዘበት መሆኑ ተገልጿል፡፡
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከንቲባ አማካሪ ጥላሁን ሮባ መንግስት ሰው ተኮር ስራዎች ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ የበጎ ፈቃድ አገለግሎት የእዚሁ አካል መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የበጋ በጎ ፈቃድ አገልገሎት፤ የ2017 የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የተሰሩ ስራዎችን መነሻ በማድረግ ጥንካሬውን በማስቀጠል ችግሮቹን በማረም ተግባራዊ መደረግ እንደሚገባው በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
በክረምት መርሃግብር በከተማዋ አዲስ ዓመት፣ መስቀል፣ ኤሬቻና ሌሎች በዓላት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሁነቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቁ በጎ ፈቃደኞች ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው ገልጸዋል፡፡
የበጎ ፈቃድ አግልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱን የተናገሩት ጥላሁን ሮባ በውጭ ሀገራት ላይ ካለን ተረጂነት በመላቀቅ የኢትዮጵያውያንን ችግር በራስ ለመፍታት አቅም ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡
የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አስራት ንጉሴ በበኩላቸው፤ በጎነት የልብ ግኝኙነትን በማጠናከር ማህበራዊና ኢኮኖሚያ ጉድለቶችን ለመሙላት ከፍተኛ አበርክቶ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ተግባራዊ እየተደረገ በሚገኘው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት 7 ዓመታት ከ42 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የበጎ ፈቃ አገልግሎት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ በጎ የሚያደርጉ እና በመርሃግብሩ የሚሳተፉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ነው ምክትል ኮሚሽነሯ የተናገሩት፡፡
የ2018 ዓ.ም የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃግብር ከ500 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞችን በ13 ዋና ዋና ፕሮግራሞች በድግግሞሽ ለማሳተፍ እቅድ የተያዘበ መሆኑ ተገልጿል። መርሃ ግብሩ ከጥቅምት 1/2018 እስከ ግንቦት 30/2018 ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በ – ሰላም ይልማ












