የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ የሊባኖስ መንግስት ሄዝቦላህን ትጥቅ ማስፈታት አለበት ሲሉ አስጠነቀቁ ።
የሊባኖስ ባለስልጣናት ከደቡባዊ ሊባኖስ የሄዝቦላህ ታጣቂዎችን ለማስወጣት የገቡትን ቃል መፈፀም አለባቸው ሲሉ ካትዝ ተናግረዋል ። በደቡባዊ ሊባኖስ ጥቃቷን አጠናክራ የቀጠለችው እስራኤል አራት የሄዝቦላህ አባላትን መግደሏን አስታውቃለች ።
ባለፈው ዓመት ህዳር በአሜሪካ አሸማጋይነት ተኩስ አቁም ስምምነት ላይ የደረሱት እስራኤል እና ሄዝቦላህ ዳግም ወደ ግጭት መግባታቸው ለቀጠናው ስጋት ነው እየተባለ ነው። ካትዝ በሰሜን እስራኤል የሚገኙ ዜጎችን ከጥቃት ለመከላከል ትልቁን የሀይል ጥቃት ለማድረግ (maximum enforcement efforts ) እንገደዳለን ብለዋል።
እስራኤል የሄዝቦላህ ጎምቱ መሪዎችን በመግደል ቡድኑ የነበረውን ጥንካሬ እንዲቀንስ ማድረጓ የሚታወስ ቢሆንም፣ ሄዝቦላህ ግን አሁንም ለእስራኤል እጅ አልሰጥም እያለ እንደሚገኝ ተንታኞች እየተናገሩ ነው።
የሊባኖስ መንግስት በበኩሉ፣ ሄዝቦላህን ትጥቅ ለማስፈታት እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልፆ፣ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ግን በተደጋጋሚ መግለጫ ማውጣቱን አስታውቋል ።
ታይምስ ላይቭ እንደዘገበው
በ-ቶማይ መኮንን












