“አንድነት ለተግባራዊ እርምጃ የአፍላ ወጣትነት እርግዝናን ለማስቆም እንተባበር!” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ያለው የጤና ፎረም ሃገር አቀፍ የአፍላ ወጣቶችና የወጣቶች ጤና ተግበራን በሀገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት ታላሚ ያደረገ መሆኑ ተገለፀ፡፡
የአፍላ ወጣትነት እርግዝናን ለማስቆም ዋና ትኩረቱ በማድረግ እየሰራ እንደሆነ ያመላከተው የጤና ሚኒስቴር በወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ላይ የሚከሰቱ የጤና እክሎችን መግታት የሚያስችል የጤና አገልግሎትን ይበልጥ ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን አመላክቷል፡፡
ስድስተኛው ሀገራዊ የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ጤና ጉባኤ በአዲስ አበባ በሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል ተካሂዷል። የጤና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በመድረኩ መንግሥት የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ባከናወናቸው ተግባራት አበረታች ውጤት ማምጣት መቻሉን ተናግረዋል።
በተለይም ባለፉት ዓመታት በወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ላይ ትኩረት ያደረገ የጤና አጠባበቅ ሥርዓት መዘርጋት ዋነኛው የሥራ መስክ መሆኑን አብራርተው የወጣቶች ያለ ዕድሜ ጋብቻ መፈጸም ለፊስቱላና ለመሰል ከባድ የጤና ጉዳቶች የመጋለጥ እድል የሚጨምር ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡
ጉባኤው ለወጣቶች ዘርፍ ከፍተኛ ጥቅምና ትርጉም ያለው መሆኑን ያመላከተ ሲሆን በወጣቶች ዙሪያ በሚከናወኑ ተግባራት የባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ አሠራር ለማጠናከር ያለመ ነውመ ተብሏል፡፡
መድረኩ የአፍላ ወጣት እርግዝና ፌስቱላን ጨምሮ የሚያደርሰው አካላዊ እና ስነ- ልቦናዊ ጉዳት ቀላል የሚባል ባለመሆኑ ትኩረት የሚያሻው ሆኖም መገኘቱን አመላክቷል፡፡ በተጨማሪም ሁሉም ዜጋ ይህን ችግር እንደሀገር ለመቅረፍ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል፡፡
በ-ማህሌት ግርማ












