ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባለፉት ጊዜያት በመዲናዋ የተከናወኑ ከተማዊ ፣ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ኩነቶች በተሳካ መልኩ በድምቀት እንዲጠናቀቁ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካላትን አመሰገኑ።
ከ25 ሺህ በላይ አለም አቀፍ ተሳታፊዎች የተሳተፉበት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ እና የአፍሪካ ካረቢያን ሀገራት መሪዎች ጉባኤ በስኬት ተጠናቀዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት ባለፉት ጊዜያት በቅደም ተከተል የተከናወኑ የአለም፣ የአህጉር እና የሀገር አቀፍ ኩነቶች፣ ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ፕሮግራሞች ለአብነትም የአየር ንብረት ለዉጥ ጉባኤ፣ መስከረም አንድ በመስቀል አደባባይ የተከናወነው የወንጌል አማኞች የአምልኮ ፕሮግራም፣ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ የተካሄዱ ህዝባዊ ሰልፎች ፣የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ ክብረ በዓላት እጅግ ወንድማማችነት፣ እህትማማችነት በሰፈነበት መንፈስ ያለ አንዳች የፀጥታ ችግር መከበሩ የህዝባችንን ጨዋነት ዳግም ያረጋገጠ ነዉ።
ሁሉንም ሃገር አቀፍና አለማቀፍ ጉባኤዎች እንዲህም ሃይማኖታዊ በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ በየደረጃዉ ያሉ አመራሮች፣ የሆቴል ባለቤቶች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምርት አምራቾችን የዋጋ ንረትና የምርት እጥረት እንዳይኖር በማድረጋቸዉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አመስግነዋል።
በተለይም የሀይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ስንቄዎች ክብረ በዓላቱ እሴታቸዉን ጠብቀዉ እንዲከበሩ በማስተባበር ረገድ ለነበራቸዉ የላቀ አስተዋፆ ምስጋና አቅርበዋል።












