የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ ለማሳካት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጎለብቱ ተግባራት ትኩረት እንደተሰጣቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በ6ኛ የፓርላማ ዘመን 5ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ 1ኛ መደበኛ ስብሰባ የመንግስታት ግንኙነት፣ ዴሞክራሲያዊ አንድነትና የሕገ-መንግስት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም የሕገ መንግስትና የፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸምን በማዳመጥ የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ተወያይቶ አጽድቋል።
በፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግሥታት ግንኙነት፣ የዴሞክራሲያዊ አንድነትና የሕገ መንግሥት አስተምህሮ ቋሚ ከሚቴ ጸሐፊ ወይዘሮ ባንችይርጋ መለሰ፤ 19ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ሕብረብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ በአርባ ምንጭ ከተማ በድምቀት መከበሩን አስታውሰዋል።
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ብዝኃነት ላይ የተመሰረተ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጎላ መልኩ በድምቀት ማክበር የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
በሕገ-መንግስትና ፌደራሊዝም ዙሪያ የዜጎችን ግንዛቤ በማሳደግ ብሔራዊ መግባባትና የህዝቦችን አንድነት የሚያጎለብቱ የአስተምህሮ ስርጸት ተግባራት ትኩረት እንደሚሰጣቸው አስረድተዋል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር በማጠቃለያቸው፤ ኢትዮጵያ በማንሰራራት ዘመን ጉዞ ላይ ናት ብለዋል።
የዜጎችን ሕብረ ብሔራዊ መግባባትና አንድነት የሚያጎለብቱ የአስተምህሮና የስርጸት ተግባራት በትኩረት እንደሚሰራባቸው አንስተዋል። 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ታላላቅ ሀገራዊ አጀንዳዎች በሚከወኑበት ወቅት የሚከበር በመሆኑ ልዩ ትርጉም እንደሚሰጠው ተናግረዋል።
በዓሉ ህብረ ብሔራዊነትን በማጎልበት የሀገርን የማንሰራራት ጉዞ በሚያሳካ መልኩ በልዩ ድምቀት እንደሚከበር ጠቅሰዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።












