ዌስትሃም ዩናይትድ አሰልጣኝ ግራሃም ፖተርን የተመለከተ መግለጫ አወጣ::
የምስራቅ ለንደኑ ክለብ ዌስትሃም ዩናይትድ የውድድር አመቱን እጅግ ደካማ በሆነ ውጤት መጀመሩን አስመልክቶ ለደጋፊዎቹ መግለጫ ሰጥቷል።
ባሳለፍነው የውድድር አመት አጋማሽ ክለቡን የተረከቡት አሰልጣኝ ግራሃም ፖተር በአዲሱ የውድድር አመት ለተሻለ ውጤት ቢጠበቁም እስካሁን በሁሉም ውድድሮች ባደረጓቸው 5 ጨዋታዎች በ4ቱ ሽንፈት አጋጥሟቸዋል።
በውጤቱ እጅግ የተከፉት ደጋፊዎች በሜዳቸው በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ጥለው ሲወጡ ታይተዋል። ዌስትሃም በመግለጫው “ክለቡ እየተመዘገበ ባለው ውጤት ደስተኛ አይደለም ያለ ሲሆን ፣የቦርድ ሃላፊዎች በተገኙበት በጉዳዩ ላይ ውይይት መደረጉን ገልጿል።
አያይዞም “ የቡድን ስብስባችን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ይረዳናል ያለ ሲሆን፣በፍጥነት አሁን ካለንበት ማሽቆልቆል መውጣት ይኖርብናል ሲል በአሰልጣኝ ግራሃም ፖተር ላይ ጫና አሳድሯል። መዶሻዎቹ በፕሪምየር ሊግ 14 አመት በተከታታይ መቆየታቸውንም በጥንካሬነት በማንሳት የተሻለ ውጤት እንዲመጣ ሁላችንም የሚጠበቅብንን መስራት ይኖርብናል ብሏል።
በአስቸኳይ ወደ አሸናፊነት እንዲመለሱ ጫና ውስጥ የገቡት አሰልጣኝ ግራሃም ፖተር የፊታችን ቅዳሜ ከክሪስቲያል ፓላስ ጋር የሚጫወቱ ይሆናል። በተከታታይም ከኤቨርተን፣አርሰናል፣ብሬንትፎርድ እና ሊድስ ዩናይትድ ጋር ፈታኝ ጨዋታ ይጠብቃቸዋል።
በ-አልፈሪድ ነስሮ












