የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የሥራ እና ሥልጠና ሥራ ከባድ፣ የብዙ አካላትን ትብብር የሚጠይቅ፣ በአንድ ተቋም ብቻ የማይሠራ፣ የኢትዮጵያን ችግሮች ለመፍታት ቁልፍ ተግባር የሚፈጸምበት መሆኑን ነው ብለዋል።
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በላይ ዘለቀ ክፍለ ከተማ የአቅመ ደካሞችን ቤት ሥራ በይፋ አስጀምረዋል።

የኢትዮጵያ አንደኛው ችግር ሥራ አጥነት ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የሥራ እና ሥልጠና ለሀገር ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ መኾኑን ገልጸዋል። የአማራ ክልል የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት እቅድ በማቀድ የተሻለ ክልል ለመፍጠር ሥራ መጀመሩንም ተናግረዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወገኖችን ቤት የመጠገን እና በአዲስ መልክ እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። 108 ቤቶችን ጠግነው፣ 70 ቤቶችን ደግሞ በአዲስ ሠርተው ማስረከባቸውን ተናግረዋል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

ከቤት እድሳት እና ሥራ ባለፈ የደም ልገሳ፣ ለተማሪዎች ቁሳቁስ ድጋፍ እንደተደረገ ነው የተናገሩት። የአዲስ ዓመትን መግባት ተከትሎ ለአቅመ ደካሞች የበዓል መዋያ ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ላሳየው በጎ ተግባር ምስጋና አቅርበዋል። በከተማዋ በርካታ የልማት ሥራዎች መሠራታቸውንም ገልጸዋል። የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ/ር) ዛሬ የተጀመረው የቤት ሥራ የዓመቱ የመጨረሻ የበጎ አገልግሎት መኾኑን ገልጸዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የኢትዮጵያውያን እንቁ ባሕል እና እሴት መኾኑን ተናግረዋል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመንግሥት ልዩ ትኩረት ሆኖ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። 15 ሚሊዮን ብር በማውጣት 41 ቤቶችን ገንብተው ማስረከባቸውንም ገልጸዋል። ዛሬ የተጀመረው ደግሞ ተጨማሪ ነው ብለዋል።
የአቅመ ደካሞች የቤት ሥራው በአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ አማካኝነት የሚሠራ ነው።












