በመላው ኢትዮጵያውያን ትብብር ግንባታው ተጠናቆ ለምረቃ የደረሰው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዳግማዊ አድዋ ሲሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርኸ (ዶ/ር) ተናግረዋል ።
በመጪው ማክሰኞ ጳጉሜ 4 የሚመረቀው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አስመልክቶ የፓናል ውይይት ተካሄዷል።
በመላው ኢትዮጵያውያን ትብብር የተገነባው ግድቡ በአብሮነትና በአንድነት ያለ ጦርነት የአድዋን ድል ዳግም መድገም የቻልንበት የጽናት ተምሳሌትና የዘመናችን ኩራት ነው ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።
የግድቡ ግንባታ በይፋ ከተጀመረበት አንስቶ ባለፉት 14 አመታት በርካታ ተግዳሮቶች ቢገጥመንም በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ንቁ ተሳትፎ እና በመንግሥት የተቀናጀ ድጋፍ ለፍጻሜ መድረስ መቻሉንም አክለው ገልጸዋል።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ህብረት ካለ ታላላቅ ነገሮችን መስራት እንደሚቻል ማሳያ ነው ያሉት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ ሞቱማ መቃሳ በቀጣይ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ተመሳሳይ ታላላቅ ፕሮጀክቶች በመስራት ኢትዮጵያን በኢኮኖሚ ማሳደግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ግድቡ ከሀይል ማመጨት ባሻገር ኢትዮጵያን ብሎም የአፍሪካ ሀገራት ያለማንም እርዳታ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ሰርተው ማጠናቀቅ እንደሚችሉ ለአለም ማሳየት የተቻለበት ፕሮጀከት ነው ያሉት ደግሞ የአፍሪካ የልህቀት አካዳሚ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዛዲግ አብርሃ ናቸው።
ግድቡ የአፍሪካ የአዲስ ዘመን ብስራት ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው ኢትዮጵያ ከክፍለ ዘመናት ረሃብና መሸማቀቅ ወጥታ በራሷ አቅም ግድቡን በመገንባት አንገቷን ቀና ማድረግ ችላለች ብለዋል።
ይህ ግድብ በድህነት ውስጥ የሚገኙ ሀገራት ብሎም ለማደግ እጣሩ ላሉ የአለም ሀገራት ማሳያ መሆኑንም ጠቁመዋል። ታላቁ የህዳሴ ግድብ ጳጉሜ 4 በታላቅ ድምቀት እንደሚመረቅ ይጠበቃል።
በ- ሰላማዊት ወልደገሪማ












