የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምርት አቅርቦትን በማሳደግ ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር እየሰራ እንደሚገኝ እና አምራቾች በቀጥታ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ በማድረግ የተሻለ የግብይት ስርዓት መፍጠር መቻሉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልፀዋል።
በዛሬዉ እለት የ2018 አዲስ ዓመት ንግድ፣ ኤግዚቢሽንና ባዛር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ እና ሌሎችም ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በአፍሪካ ህብረት የገበያ ማዕከል በይፋ ተጀሞሯል።

በቅርቡ ተመርቀዉ ስራ የጀመሩ የገበያ ማዕከላትም በዓል ጠብቀዉ ብቻ ሳይሆን ዓመቱን ሙሉ በአዘቦት ቀን ጭምር አምራችና ሸማቹን በቋሚነት እንዲያገበያዩ ይደረጋል፡፡ ሸማቾች ላልተገባ የዋጋ ጭማሪ ሳይጋለጡ ወደነዚ ስፍራዎች ጐራዉ ብለዉ እንዲሸምቱ እና አምራቾች በቀጥታ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርበዋል ከንቲባዋ ።
የበዓል ባዛሩ፣ በአፍሪካ ህብረት፣ በ4 ኪሎ ችሎት የገበያ ማዕከላት ጨምሮ በሁሉም ክፍለ ከተምች በሚገኙ የገበያ ማዕከላት መካሄድ ጀሞሯል ።
በባዛሩ የተለያዩ የግብርና፣ የኢንዱስትሪ እንዲሁም ለበዓል ወቅት የሚያስፈልጉ ሸቀጦች በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ማህበረሰብ ቀርበዋል ።
በኤዚቢሽንና ባዛሩ መክፈቻ ላይ የተገኙት ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው፣ በገበያ ማዕከላቱ ለበዓል ብቻ ሳይሆን ሁሌም አምራችና ሸማቹ እንዲገበያይበት ይደረጋል፡፡ ሸማቹ ህብረተሰብም በአቅራቢያዉ ወደሚገኙ ማዕከላት እየሄደ እንዲገበያይ ጥሪ አቅርበዋል ሲል የከንቲባ ጽ/ቤት ያደረሰን መረጃ ያመለክታክል፡፡












