የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ እና የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ታሪካዊ ነው ያሉትን ውይይት አደረጉ።
የመሪዎቹ ውይይት የኒው ደልሂ እና ቤይጂንግ ግንኙነት ከትላንቱ ዛሬ መልካም እየሆነ መምጣቱንም ያሳያል ተብሎለታል። ሺ እና ሞዲ በሻን’ካይ ትብብር ጉባዔ ላይ በቲያንጂን ነው የተገናኙት።
መሪዎቹ በSCO ጉባዔ ጎን ለጎን ባደረጉት ውይይት ለረዥም ጊዜ የዘለቀውን የድንበር ላይ ውዝግብ ችላ ብለው ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን ለመከተል እና ግንኙነታቸውን ለማሻሻልም ቃል ገብተዋል ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ከሰባት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ወደ ቻይና ብቅ ያሉት። ሺ ጂንፒንግ እና ናሬንድራ ሞዲ በሩሲያ የካዛኑ የብሪክስ ጉባዔ ላይ በ2024 የተገናኙ ሲሆን የድንበር ግጭቶችን በመግታት ለሁለቱም አገራት ህዝቦች ጥቅም ለመስራት ውጥን ይዘው መለያየታቸው አይዘነጋም።
”ግንኙነታችን ወደ በጎው አቅጣጫ እየተጓዘ ነው። በድንበር አካባቢም ሰላም እና መረጋጋቱ አለ።” ብለዋል ናሬንድራ ሞዲ። ሞዲ የሚሉት “የሁለቱም አገራት 2.8 ቢሊዬን ህዝብ ፍላጎትና ጥቅም ከትብብራችን ጋር አብሮ ይቃኛል።” ነው።
የጋራ ጥቅምን ባከበረ እና አንዱ ሌላውን ሳይጎዳ በትብብር መስራት የደልሂን እና ቤይጂንግን ዲፕሎማሲ ብቻም ሳይሆን የዓለምን ፖለቲካም መታደግ ይችላል ተብሎለታል የሺ ጂንፒንግና ናሬንድራ ሞዲ ውይይት።
አር ቲ እንዳስነበበው
በ -ቢኒያም ካሴ












