የማዳበሪያ ፋብሪካው ግንባታ ፕሮጀክት ስምምነት ለኢትዮጵያዊያን የአዲስ ዓመት ዋዜማ ብስራት ነው ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ገለፁ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና ዳንጎቴ ግሩፕ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ለሚገነባው የማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክት ግንባታ ስምምነት ተፈራርመዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የግንባታ ስምምነቱ የግብርናውን ዘርፍ ለመደገፍ አይተኬ ሚና እንደሚኖረው ተናግረው ኢትዮጵያ በከፍተኛ ወጪ የምታስገባውን ማዳበሪያ በማስቀረት የውጭ ምንዛሪን ለማዳን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል ብለዋል።
የግብርና፣ የኢንዱስትሪና የማዕድን ዘርፍ ልማትን በማገዝ በኩል የጎላ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም ነው የገለፁት። የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት በማፋጠን፣ ለስራ ዕድል ፈጠራና ፋብሪካው በሚገነባበት አካባቢ ያለውን ልማት ለማነቃቃት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በቅርቡ እንደሚመረቅ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ የማዳበሪያ ፋብሪካው ሌላኛው ታላቁ ህዳሴ ተደርጎ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።












