ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና በዳንጎቴ ግሩፕ መካከል የማዳበሪያ ማምረቻ ኮምፕሌክስ የድርሻ ስምምነት በዛሬው ዕለት መፈረሙን ይፋ አድርገዋል።

ይህን ተከትሎ የዳንጎቴ ግሩፕ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አሊኮ ዳንጎቴ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም፤ ኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ የሌላት እና ከውጪ ሀገራት በግዥ የምታስገባ መሆኗን አውስተው ኢትዮጵያ ከዓለም ግንባር ቀደም አምራቾች አንዷ የሚያደርጋትን ግዙፍ የአፈር ማዳበሪያ ማምረቻ ለመገንባት ዛሬ ስምምነት መፈረሟን ገልጸዋል።
ይህን በዓመት ሦስት ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካ በተያዘለት ጊዜና ጥራት እንደሚያከናውኑም አረጋግጠዋል። ኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያ የምታስገባ ገዥ ሳትሆን የራሷን ፍላጎት ከመሸፈን ተሻግራ ለሌሎች ሀገራት ላኪ እንደምትሆንም አስረድተዋል።
የአህጉራችን ኩራት እና የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ በሆነችው ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በሲሚንቶ ማምረት ዘርፍ በኢንቨስትመንት መሳተፋቸውንም አውስተዋል። አሁን ደግሞ በማዳበሪያ ማምረቱ ሂደት ኢትዮጵያ በቂ ግብዓት ያለባት ሀገር መሆኗን አንስተው፤ ለዘርፉ ስኬታማነት በትጋት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።












