@NBCEthiopia
ሩሲያ በዛሬው ዕለት የድሮን እና የሚሳይል ናዳን በዩክሬን ላይ ማዝነቧ ተሰማ፡፡
የዩክሬን አየር ኃይል እንዳረጋገጠው ሞስኮ በኪዬቭ ሰማይ ስር 598 የድሮን ጥቃት እና 31 የሚሳይል ጥቃት መፈጸሟን አረጋግጧል፡፡ ሩሲያ ለሊቱን የፈፀመችው ይህ የድሮንና የሚሳኤል ጥቃት ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከአሜሪካን አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ ጋር በአላስካ ከተወያዩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል።

የኪዬቭ ወታደራዊ አስተዳደር በበኩሉ በጥቃቱ ሕጻናት ሕይወታቸውን እንዳጡም ተናግሯል። የመኖርያ ሕንጻዎች ወድመዋል በኪዬቭ የሚገኙት የአውሮፓ ሕብረት ቢሮ ሲወድም የእንግሊዘኛ ቋንቋ ማዕከሉ ብርቲሽ ካውንስልም ጉዳት ደርሶበታል፡፡
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስም በጥቃቱ አርባ ስምንት ሰዎች ሲቆስሉ አስራ አራት ሰዎች ለሕልፈተ ሕይወት መዳረጋቸው ተጠቅሷል፡፡ ከሟቾቹ መካከልም አራቱ ሕጻናት መሆናቸው ነው የተነገረው፡፡ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪዬር ስታርመር በበኩላቸው የሩሲያ ድርጊት ሆን ብሎ ሰላምን ማደናቀፍ እና ከስምምነት ለመሸሽ የሚደረግ ሁኔታ ነው ብለውታል፡፡

ስታርመር ፕሬዝዳንት ፑቲን ሕጻናት እና ንጹሐንን እየገደለ ነው የሚል ወቀሳንም ሰንዝረዋል፡፡ በዋና ከተማዋ ኪዬቭ እንዲሁም በርካታ ህንጻዎች መውደማቸውንና የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ከፍርስራሽ ውስጥ ሰዎችን ለማውጣት ርብርብ እያደረጉ መሆኑም ታውቋል፡፡ ጥቃቱ እጅግ ከባድ በመሆኑም ኪዬቭ ሐዘኗን ለመግለጽ ስትል በነገው ዕለት ሰንደቅ ዓላማዋ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ወስናለች፡፡
በተደጋጋሚ አሜሪካን ጨምሮ የአውሮፓ ሕብረትን እና ዓለም ዓቀፉ ማሕበረሰብን ሲማጸኑ የነበሩት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪም ፑቲን ከውይይት ይልቅ የድሮን እና የሚሳይል ጥቃትን አማራጭ አድርገዋል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
በ-ፍቅረሚካኤል ዘየደ












