በተያዘው የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ አቅም በማሳደግ ከ9 ነጥብ 4 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለማስገኘት ዕቅድ መያዙን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።
በተጠናቀቀው የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ዘርፍ ትልልቅ እመርታዊ ስኬቶችን ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።
የኢትዮጵያን የገበያ መሰረተ ልማት ስብራት ለመጠገን በተሰራው ስራ ከ1 ሺህ 500 በላይ የቅዳሜና እሁድ የገበያ ማዕከላትን በማደራጀት አምራችና ሸማቹ የሚገናኝበት ምቹ ምኅዳር መፈጠሩን አብራርተዋል።
በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የአገልግሎት ሥርዓት በመዘርጋት የንግዱ ማህበረሰብ ባለበት ቦታ ሆኖ በኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት እንዲያገኝ እየተደረገ ነው ብለዋል። የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎትን ይበልጥ ለማሳለጥም በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ የገበያ ተወዳዳሪነት አቅም በማሳደግ ከወጪ ንግድ 8 ነጥብ 3 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጸው የማዕድን፣ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ የኤሌክትሪክ ግብይት የምርት ውጤቶች ለወጪ ንግድ ገቢ መገኘት ቁልፍ ሚና ማበርከታቸውንም አስታውሰዋል፡፡
በሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን የገበያ የድርድር ሂደት 20 አባል ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር የሁለትዮሽ የገበያ ድርድር ማድረግ እንደሚፈልጉ መግለፃቸውን አንስተዋል። በመጪው መስከረም በጄኔቫ በሚካሄደው 6ኛው የስራ ላይ ቡድን ስብሰባ ኢትዮጵያን የድርጅቱ አባል ለማድረግ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን በመላክ በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነትም በመጪው መስከረም ወር ሁለተኛ ሳምንት ውስጥ የመጀመሪያውን ንግድ ለመጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል። በኢትዮጵያ የጥራት መንደር የምርት ጥራትን ማስጠበቅ የሚያስችል የላቀና የተሳለጠ የወጪና ገቢ ምርት ጥራት ፍተሻ እየተከናወነ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የንግድ መዋቅሩን አቅም ማሳደግ፣ የገበያ ቁጥጥርን ማጠናከር፣ ያልተገባ ዋጋ ጭማሪን የማረቅና የምርት ክምችን የማስተካከል ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል።












