የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ “ሁቲ እስራኤልን በማጥቃቱ ከባዱን ዋጋ እየከፈለ ነው” አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “መላ ቀጠናው የእስራኤልን ጥንካሬና ቁርጠኝነት እየተመለከተው ነው” በሚል መግለጫ ሰጥተዋል። በሌላ በኩል ኢራን እና የጋዛው ሃማስ እስራኤል በሰንዓ የመን የፈጸመችውን የአየር ጥቃት በጥብቅ አውግዘዋል።
ኔታንያሁ ስለጦራቸው ጥንካሬ በኩራት ቢያስረዱም፣ ሁቲዎች በተደጋጋሚ የቴል አቪቭን አየር ክልል መጣስ የቻለ ሚሳዔል መታጠቃቸው ግን የሚካድ እንዳልሆነ ታውቋል። እስራኤልን ለማጥቃት “እቅድ ያለውን ሁሉ እናጠቃለን” ያሉት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር “ላጠቃንም ምላሻችን ይከፋል” ብለዋል።
የእስራኤልን ጥቃት ተከትሎ የተለያዩ አገራት እና ተቋማት በኔታንያሁ መንግስት ላይ ትችት የሰነዘሩ ሲሆን ድርጊቱ ዓለም አቀፍ መርህን የሚጥስ ነው ብለውታል። ሃማስ በሰንዓ ፕሬዚዳንታዊ ቤተመንግስት እንዲሁም በንጹሃን መኖሪያዎች ላይ የደረሰው አደጋ እስራኤል የአረብ አገራትን ሉዓላዊነት እና ዓለም አቀፍ ህግጋትን መጣስዋን ያሳያል ብሎታል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይም እስራኤል በየመን የጦር ወንጀል ፈጽማለች በሚል ድርጊቱን አውግዘውል።
እስራኤል ጥቃቱን ለመፈጸም ከአስር በላይ ተዋጊ ጀቶችን ተጠቅማለች የተባለ ሲሆን ራሳቸውን “አንሳራላህ” ብለው የሚጠሩት ሁቲዎችም የጋዛ ቀውስ እስካልቆመ ድረስ እስራኤል ላይ ጥቃት ማድረሳችንን ችላ አንለውም የሚል መግለጫ ሰተዋል።
ዘገባው የአልጀዚራ እና ዘ ታይምስ ኦፍ እስራኤል ነው
በ-ቢኒያም ካሴ












