አዲስ አበባ ቪ አይ ፒ ላውንጅ እና ሬስቶራንት ውስጥ በሁለት ግለሰቦች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የሰው ህይወት ማለፉን ተከትሎ ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል።
ድርጊቱ የተከሰተው ነሀሴ 07 ቀን 2017 ዓ/ም በግምት ከቀኑ 7 ሰዓት አካባቢ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 በተለምዶ “ሃያ ሁለት” በሚባለው አካባቢ በሚገኘው” ቪ አይ ፒ ላውንጅ” ሆቴል ውስጥ ነው።
በዕለቱ በድርጅቱ በጥበቃነት (ጋርድነት) እና በሙዚቃ (ዲጄ) ሰራተኝነት ተቀጥረው በሚሰሩ ልደቱ አያኖ እና ናትናኤል ልዑል በተባሉ ግለሰቦች መካከል ምክንያቱ ባልታወቀ አለመግባባት በተፈጠረ ጸብ ምክንያት ናትናኤል ልዑል የተባለው ግለሰብ ጭንቅላቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረስበት መሆኑን ፖሊስ በስፍራው ደርሶ ካሰባሰበው መረጃ ማረጋገጥ ችሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርብ ርቀት የነበሩ ሰዎች ተጎጂውን ወደ ህክምና በመወሰድ ልደቱ አያኖ የተባለው ግለስብ ከአካባቢው እንዳይሸሽ እየጠበቁት በነበረበት አጋጣሚ፣ ድብደባው በተፈፀመበት አልጋ ክፍል ቁጥሩ 505 አምስተኛ ፎቅ ላይ ባለ ክፍል ውስጥ ገብቶ በሩን ከውስጥ በመዝጋት ከክፍሉ ባለ መስኮት ወደ መሬት ወድቆ ጉዳት ደርሶበት ወደ ሆስፒታል ተወስዶ እርዳታ እየተደረገለት ህይወቱ ያለፈ ሲሆን ትክክለኛ የአሟሟቱን ሁኔታ ለማወቅ ምርመራው ቀጥሏል።
ከባድ ጉዳት የደረሰበት ናትናኤል ልዑል የተባለው ግለሰብ አሁንም በህክምና ተቋም ውስጥ ተኝቶ ክትትል እየተደረገለት ይገኛል።
በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማስረጃ የማሰባሰብ ስራዎችን በመስራት እና የአስክሬን ምርመራ ውጤት በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ የገለፀው የአዲስ አበባ ፖሊስ፤ የምርመራ ስራው እንደተጠናቀቀ ሙሉ መረጃውን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
ከዚህ የወንጀል ሁኔታ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ግለሰቦች በማህበራዊ ሚዲያ የሚያስራጩት መረጃ ተገቢነት የሌለው መሆኑን ያስታወቀው ፓሊስ ሀሰተኛ መረጃ፣ የህግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል መሆኑን ጨምሮ አስታውቋል።
ከትክክለኛው የመረጃ ምንጭ ውጭ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚለቀቁ መረጃዎች እውነተኛነታቸዉን የሳቱ መሆኑን ህብረተሰቡ ተገንዝቦ ለችግሩ የመፍትሄ አካል እንዲሆን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ጥሪውን አቅርቧል።












