ከሰባት ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ከመደበኛ ሰራተኞች ጋር በመቀናጀት አደጋ የመከላከል ስራ እየሰሩ መሆኑን የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር አህመድ መሃመድ እንዳሉት፤ የአደጋ መከላከል ስራ ፍጹም በሆነ ሞራልና ሰብዓዊነት የሚሰራ ተግባር ነው። ይህን ተከትሎ ከአራት ሺህ በላይ ነባር በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ለበርካታ ዓመታት ተቋሙን በእውቀታቸውና በጉልበታቸው ሲደግፉ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።
በጎ ፈቃደኞቹ ከተቋሙ ቋሚ ሰራተኞች ጋር በመቀናጀት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ አደጋ እንዳይከሰትና በአደጋ ወቅትም የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ሲሰሩ መቆየታቸው ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈ ህብረተሰቡ አደጋን ቀድሞ መከላከል እንዲችል የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከሶስት ሺህ በላይ የሚሆኑ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ሰልጥነው ወደ ስራ መግባታቸውን አስታውቀዋል።
ኮሚሽነሩ አክለውም፤ አሁን ላይ ከሰባት ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ከመደበኛ ሰራተኞች ጋር በመቀናጀት አብረው እየሰሩ መሆኑን አብራርተዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡












