የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ የህገ ወጥ ገንዘብ ዝውውር ወንጀልን መከላከል ቡድን ዓመታዊ ጉባኤ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ሃብትን ህጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለሚደረገው ጥረት ተጨማሪ አቅም የሚፈጠርበት መሆኑን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡
ኢትዮጵያ ከነሐሴ 16 እስከ ነሐሴ 24 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ የህገ ወጥ ገንዘብ ዝውውር ወንጀልን መከላከል ቡድን ዓመታዊ ጉባዔን ታስተናግዳለች።
የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሙሉቀን አማረ እንደገለጹት፤ ጉባዔውን ማስተናገድ የሚያስቸል በቂ ዝግጅት እንደተደረገ እንዲሁም በጉባኤው ከ21 አባል ሀገራት የተውጣጡ የፋይናንስ ደህንነት ተቋማት፣ አንድ ታዛቢ ሀገር እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል።
በወንጀል ድርጊት የተገኘ ሃብትን ህጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎች ድንበር ተሻጋሪ እና የሚያስከትሉት ተጽዕኖ ዓለም አቀፍ መሆኑን ተናግረዋል። ጉባዔው ቀጣናዊ ትብብርን ለማጠናከርና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ከማገዙ ባሻገር ምክረ ሀሳቦች የሚቀርቡበት መሆኑንም አመላክተዋል።
ጉባዔው በወንጀል ድርጊት የተገኘ ሃብትን ህጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለሚደረገው ጥረት ተጨማሪ አቅም የሚፈጠርበት መሆኑን አንስተዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡












