በኢትዮጵያ ያለውን ከፍተኛ የፀሐይ ኃይል ልማት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን የዓለም አቀፍ የፀሐይ ኃይል ጥምረት (አይ.ኤስ.ኤ.) አስታወቀ።
የዓለም አቀፍ የፀሐይ ኃይል ጥምረት ዋና ዳይሬክተር አሺሽ ከሀና እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በፀሐይ ኃይል አማራጭ ከፍተኛ የመልማት ጸጋ ያላት ሀገር ናት።
ለዚህ ይረዳ ዘንድ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የኢትዮጵያን የፀሐይ ኃይል ልማት ለማገዝ በሚያስችል የፕሮጀክትና የፖሊሲ ትብብር ላይ በጋራ ለመስራት የማዕቀፍ ስምምነት መደረጉን ገልጸዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ 400 ሜጋ ዋት የፀሐይ ኃይል ማመንጨት የሚያስችል ፕሮጀክት ለመገንባት የተጀመረውን ጥረት ለማገዝ ቁርጠኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል። በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ቅጥር ግቢም 100 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ የመኪና ማቆሚያ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ጣሪያ ፕሮጀክት በመገንባት ለአገልግሎት መብቃቱን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የዓለም አቀፍ የፀሐይ ኃይል ጥምረት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂ የልህቀት ማዕከል ኢትዮጵያዊያን ሙያተኞችን እያሰለጠነ እንደሚገኝ አንስተዋል። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በፀሐይ ኃይል ልማት ዘርፍ የግሉን ዘርፍ የኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሳደግ ጉልህ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡












