በመቶ ሺ የሚቆጠሩ እስራኤላውያ የጋዛ ጦርነት እንዲያበቃና ታጋቾች እንዲለቀቁ የሚጠይቅ ሰፊ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ በቴልአቪቭ አደባባይ አካሄዱ።
ከጥቅምት 2023 ወዲህ በእስራኤል ከተደረጉ ትላልቅ ሰልፎች መካከል አንዱ ነው በተባለው በዚህ የተቃውሞ ሰልፍ የእስራኤል ጦር በጋዛ እያካሄደ ያለውን ጦርነት እንዲያቆም ብሎም በሃማስ ታግተው የሚገኙ እስራኤላውያን እንዲለቀቁ ከስምምነት እንዲደረስ ጥሪ ቀርቧል።
ሰልፉ የተዘጋጀው በታጋቾች እና በጠፉ ቤተሰቦች ፎረም በጋራ ሲሆን፣ የእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ የሚያደርገው ጥቃት የቀሩትን ታጋቾች ህይወት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ይህ የተቃውሞ ማዕበል ከሳምንት በፊት የእስራኤል መንግስት ጋዛን ለመቆጣጠር ያጸደቀውን አዲስ ወታደራዊ ዘመቻ በመቃወም የተካሄደ ሲሆን መንግስት የወሰነው እርምጃ ታጋቾችን ለማስለቀቅ ከማገዝ ይልቅ ህይወታቸውን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ሰልፈኞቹ ገልጸዋል ።
በቴል አቪቭ በሚገኘው “የታጋቾች አደባባይ” የተሰበሰበው ሰፊ ሕዝብ በርካታ መፈክሮችን በማሰማት ጦርነቱ እንዲያበቃ ጠይቀዋል ።
“ሁሉንም ወደ ቤታቸው መልሱ! ጦርነቱን አቁሙ!” የሚሉት በስፋት በሰልፈኞቹ የተሰሙ የተቃውሞ ድምጾች ናቸው። “የእስራኤል መንግስት ፍትሃዊወእን ጦርነትን ወደ ትርጉም የለሽ ጦርነት ለውጦታል” ሲሉም ሰልፈኞቹ መንግስትን ተችተዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የተቃውሞ ሰልፉን በመተቸት “ሰልፉ የሃማስን አቋም እንደሚያጠነለናክር እና የታጋቾችን የመለቀቅ ሂደት እንደሚያዘገየው” ተናግረዋል።
ይህ ሰልፍ መንግስት በጋዛ እያደረገ ያለውን ወታደራዊ ዘመቻ እንዲያቆም ጫና ለማድረግ አንድ ቀን ሙሉ ከዘለቀው አገር አቀፍ የተቃውሞ አድማ በኃላ የተደረገ ነው። መንገዶች፣ የንግድ ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች በአድማውና በተቃውሞ ሰልፉ ምክንያት ተዘግተዋል። ፖሊስም መንገድ ዘግተዋል በተባሉ ሰልፈኞች ላይ እርምጃ በመውሰድ በርካታ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል ።
በዚህ ሰፉ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ ወደ 500ሺ የሚጠጉ ሰዎች መሳተፋቸው የተገለፀ ሲሆን ከአውሮፓውያን 2023 ወዲህ ከተደረጉ ሰልፎች መካከል ብዙ ሰዎች የተገኙበት መሆኑ ተነግሯል ።
በአሁን ሰአት በጋዛ 49 ታጋቾች እንዳሉ የሚታሰብ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 27ቱ መሞታቸውን የእስራኤል ጦር መግለጹ ይታወሳል ።
ዘገባው የቢቢሲ እና ዘጋርዲያን ነው
በ ሰላማዊት ወልደገሪማ












